አክሲዮን ማህበሩ በድሬዳዋ አስተዳደር ለተማሪዎች የመማሪያ ቁሶችን ድጋፍ አደረገ

ድሬዳዋ፤ መስከረም 9/2017(ኢዜአ):- በድሬዳዋ የሚገኙ ተቋማት ለትምህርት ዘርፍ እና ለትምህርት ጥራት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የአስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አቡበከር አዶሽ ገለፁ።

ድሬዳዋ የሚገኘው ናሽናል ሲሚንቶ አክስዮን ማህበር ከአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የመማሪያ ቁሶችን ለተማሪዎች ድጋፍ አድርጓል።

ማህበሩ የትምህርት መማሪያ ቁሶቹን ድጋፍ ያደረገው በድሬዳዋ ገጠርና ከተማ በሚገኙ 11 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን ለሚከታተሉ አንድ ሺህ ህፃናት ነው።

የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አቡበከር አዶሽ እና የናሽናል ሲሚንቶ አክስዮን ማህበር ሥራ አስፈጻሚ ዛሬ ለተማሪዎቹ ድጋፉን አበርክተዋል።

በዚሁ ወቅት የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቡበከር እንደተናገሩት፤ በድሬዳዋ የሚገኙ ዘርፍ መስሪያ ቤቶች እና የተለያዩ የግል ተቋማት የትምህርት ስራውን ስኬታማ ለማድረግ የጀመሩት ድጋፍ አበረታች እና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው።

በተለይ ናሽናል ሲሚንቶ አክስዮን ማህበር የትምህርት መማሪያ ቁሶችን በማበርከትና በተማሪዎች ምገባ ላይ እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የአክስዮን ማህበሩ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሚስተር ሊዕኡ ጀሽንግ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ማህበሩ በትምህርት ዘርፍ ድጋፍ በማድረግ ትውልድን ለመገንባትና ለማነፅ በሚከናወኑ ሥራዎች ላይ የበኩሉን ሚና ለመወጣት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል።

በዛሬው ዕለትም በ1 ሚሊዮን 246 ሺህ ብር የተገዙ ቦርሳዎች፣ ደብተሮች፣ እስክሪብቶዎች እና እርሳሶች ለ11 ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ማበርከቱን ተናግረዋል።

የአክሲዮን ማህበሩ ምክትል  ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ቢፍቱ መሐመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ማህበሩ ለአካባቢው ማህበረሰብ ከፈጠረው የሥራ ዕድል በተጨማሪ ማዕድ በማጋራት፣ የአረጋውያንን ቤቶች በመገንባት እና በትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምገባ ላይ በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።

ወላጆች ህፃናትን ወደ ትምህርት ቤቶች የማምጣት ኃላፊነታቸውን እና ግዴታቸውን እንዲወጡም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በድጋፍ መስጠት ስነስርዓት ላይ የተማሪዎች ወላጆች እና የየወረዳ ትምህርት ማስተባበሪያ አመራሮችም ተሳታፊ ሆነዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም