ማህበሩ በኦሮሚያ ክልል ሰባት ዞኖች ተግባራዊ የሚሆን ፕሮጀክት ይፋ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ማህበሩ በኦሮሚያ ክልል ሰባት ዞኖች ተግባራዊ የሚሆን ፕሮጀክት ይፋ አደረገ
ጅማ፤ መስከረም 9/2017(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች ችግር ያጋጠማቸውን ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ አደረገ።
ማህበሩ ከአሜሪካ ዓለም ዓቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩ.ኤስ.ኤይድ) ጋር በመተባበር በክልሉ የተለያዩ ዞኖች ለ1 ሺህ 500 አባወራዎች መኖሪያ ቤት መስሪያ እና የመቋቋሚያ ድጋፍ መስጠት የሚያስችል ፕሮጀክት ነው ዛሬ ይፋ ያደረገው።
ለፕሮጀክቱ 300 ሚሊዮን ብር የተመደበ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ በተለያዩ የክልሉ ሰባት ዞኖች ተግባራዊ እንደሚደረግም ተገልጿል።
በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ጎሳ አበራ እንዳሉት፣ በፕሮጀክቱ በቡኖ በደሌ፣ በኢሉ አባቦር፣ በሆሮ ጉድሩ፣ በምዕራብ ወለጋ፣ በምዕራብ ጉጂ፣ በቄለም ወለጋና በምስራቅ ወለጋ ዞኖች ለተፈናቃይ ወገኖች መኖሪያ ቤት መገንቢያና ማቋቋሚያ ድጋፍ ይደረጋል።
በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ መሀመድ ጀማል በበኩላቸው ማህበሩ በክልሉ በተለያየ ምክንያት ችግር ያጋጠማቸውን ወገኖች እየደገፈ መሆኑን አንስተዋል።
በተለያየ ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም እና ለመደገፍ ማህበሩ እያደረጋቸው ያሉ ተግባራትን እንደሚያጠናክር ነው የገለጹት።
ማህበሩ ባለፈው ዓመትም በክልሉ አምስት ዞኖች ለ1 ሺህ 900 ወገኖች ቤት መገንባቱንና የማቋቋሚያ ድጋፍ ማድረጉም ተመልክቷል።
በመርሃግብሩ ላይ ከተለያዩ ዞኖች የመጡ የቀይ መስቀል ሀላፊዎች፣ የቡሳ ጎኖፋ ጽህፈት ቤት ተወካዮች እና የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች ተገኝተዋል።