ቀጥታ፡

የመጋዘን ደረሰኝ ፋይናንስ ስርዓት የምርት ብክነትን በመቀነስ የአምራቹን ገቢ ለማሳደግ የሚያስችል ነው - የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ መስከረም 9/2017(ኢዜአ):-  የመጋዘን ደረሰኝ ፋይናንስ ስርዓት የምርት ብክነትን በመቀነስ የአምራቹን ገቢ ለማሳደግ የሚያስችል መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ።

የመጋዘን ደረሰኝ የፋይናንስ ስርዓት በመጋዘን የተቀመጠን የግብርና ምርት በመጠቀም ተገልጋዮች ከገንዘብ ተቋማት ብድር የሚያገኙበት ሥርዓት ነው።

በዚሁ ጉዳይ ላይም የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ምርት ገበያና ከተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ውይይት አካሂዷል።

በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የመሰረተ ልማትና ግብዓት ዘርፍ አማካሪ ዳንኤል ኦላኒ፤ የመጋዘን ደረሰኝ የፋይናንስ ስርዓት የግብርና ምርትን በወቅቱ በመሰብሰብና ብክነትን በመቀነስ የአርሶ አደሩን ገቢ ለማሻሻል የላቀ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ ከአምራች ኢንዱስትሪና ሕብረት ስራ ማኅበራት ጋር የገበያ ትስስር በማስገኘት ቀጣይነት ያለው ጠቀሜታ እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል። 

በመጋዘን ከሚያከማች የግብርና ምርት በተሻለ ዋጋ በመሸጥና ከፋይናንስ ተቋማት በሚገኝ የገንዘብ ብድር አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል።


 

በኢትዮጵያ ምርት ገቢያ የመጋዘን ደረሰኝ ሥርዓት ስራ አስኪያጅ ብርሃኑ ጥሩነህ፤ የስንዴና አኩሪ አተር የግብርና ምርቶች ወደ ሥርዓቱ መግባታቸውን ተናግረዋል።

ቀጣይም በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ባሉ 25 የምርት ገበያ ቅርጫፎችና 80 መጋዘኖች ተጨማሪ የግብርና ምርቶችን ወደ ስርዓቱ ለማስገባት እየተሰራ ነው ብለዋል። 

የሲዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኃይሉ ኢተራ፤ የመጋዘን ደረሰኝ ፋይናንስ ስርዓቱ የግብርና ምርት ግብዓት አቅርቦትን ለማሳለጥ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

በተጨማሪም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ጥራቱን የጠበቀ የግብርና ምርት እንዲያገኙ በማድረግ የግብዓት ፍላጎታቸውን ቀጥታ ከመጋዘን እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።  

በቀጣይም የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሁኔታ ቢያመቻች ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም