በአዲስ አበባ የውሻ እብድት በሽታ ክትባት መሰጠት ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ የውሻ እብድት በሽታ ክትባት መሰጠት ተጀመረ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 9/2017(ኢዜአ):- በአዲስ አበባ የውሻ እብድት በሽታ ክትባት የመስጠት ዘመቻ ተጀመረ።
የክትባት ዘመቻው ከቬ.ኤስ.ኤፍ ጀርመኒ ከተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር የጀመረው ሲሆን በመዲናዋ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች ከ16 ሺህ ለሚልቁ ባለቤት አልባ ውሾች የሚሰጥ መሆኑ ታውቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን የእንስሳት በሽታ መከላከልና ቁጥጥር ቡድን መሪ የሺዳኜ በላይሁን፤ የውሻ እብድት በሽታ ተገቢው ህክምና ካልተሰጠው ገዳይ በሽታ መሆኑን ገልጸዋል።፡
በመሆኑም በመዲናዋ ለባለቤት አልባ ውሾች የክትባት ዘመቻ መሰጠት ተጀምሯል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የቪ.ኤስ.ኤፍ ጀርመኒ ዳይሬክተር መርከብ በላይ (ዶ/ር)፤ እ.አ.አ. ከ2022 ጀምሮ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በመተባበር የእንስሳትን ጤንነትና ደኅንነት መጠበቅ የሚያስችል ፕሮግራም ተቀርፆ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ህብረተሰቡም የውሾችን የመኖሪያ ንጽህና በመጠበቅ እና በየዓመቱ በማስከተብ የውሻ እብድት በሽታን ቀድሞ መከላከል አንደሚጠበቅበት አስገንዝብዋል።
ኢትዮጵያ የውሻ እብድት በሽታን ሙሉ በሙሉ በማጥፋት ለቅድመ መከላከልና ለውሻ ጤንነት ጥበቃ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑ ታውቋል።