የኢጋድ አባል አገራት ዘላቂ የቱሪዝም ፍኖተ ካርታ የቀጣናውን ሃብት በጋራ አልምቶ ለመጠቀም ጥሩ መሰረት የሚያኖር ነው- የኢጋድ ዋና ፀሐፊ - ኢዜአ አማርኛ
የኢጋድ አባል አገራት ዘላቂ የቱሪዝም ፍኖተ ካርታ የቀጣናውን ሃብት በጋራ አልምቶ ለመጠቀም ጥሩ መሰረት የሚያኖር ነው- የኢጋድ ዋና ፀሐፊ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 9/2017(ኢዜአ):- የኢጋድ አባል አገራት ዘላቂ የቱሪዝም ፍኖተ ካርታ የቀጣናውን ሃብት በጋራ አልምቶ ለመጠቀም ጥሩ መሰረት የሚያኖር መሆኑን የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ገለጹ።
የዓለም ቱሪዝም ቀንን ምክንያት በማድረግ ላለፉት ሶስት ቀናት ሲካሄድ የነበረው የኢጋድ አባል አገራት የቱሪዝም መድረክ የአባል ሀገራቱን የ10 ዓመት ዘላቂ የቱሪዝም ፍኖተ ካርታ ይፋ በማድረግ ተጠናቋል።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግስታት ባለስልጣን /ኢጋድ/ አባል አገራትን ማዕከል ያደረገው የቱሪዝም ፍኖተ ካርታ ከፈረንጆቹ 2024 እስከ 2034 የሚተገበር ይሆናል።
የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፤ ቀጣናው በተፈጥሯዊና ባህላዊ መስህቦች የታደለና እንግዳ ተቀባይ ማህበረሰብ ያቀፈ መሆኑን አንስተዋል።
በዕለቱ ይፋ የተደረገው የቱሪዝም ፍኖተ ካርታም በአፍሪካም ሆነ በተቀረው ዓለም ተወዳዳሪና ዘላቂ ዘርፍ እንዲሆን ማስቻል መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ አባል አገራት የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ይፋ ማድረጋቸው ደግሞ ለዘርፉ እድገትና የህዝብ ተጠቃሚነት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
የ10 ዓመቱ ፍኖተ ካርታ የሀገራቱ ለፖሊሲ አውጪዎች ግብዓት የሚሆን እንዲሁም የቀጣናውን የቱሪዝም አቅም በተቀናጀ አግባብ ለማልማት የሚያግዝ መሆኑን ነው የተናገሩት።
የኢጋድ ቀጣና የተፈጥሮ ሀብትና ብዝሀ ፀጋ የተቸረው በመሆኑ በማልማትና ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ተገቢ መሆኑንም ዋና ጸሃፊው አንስተዋል።
ለዚህም የአባል አገራቱ ትብብርና የተቀናጀ የልማትና የሰላም ጥረት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህ ረገድ ኢጋድ አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የኢፌዴሪ የቱሪዝም ሚኒስትሯ ናሲሴ ጫሊ፤ አፍሪካ የቱሪዝም መስህቦች እምቅ ሃብት ያላት አህጉር ብትሆንም በዘርፉ እምብዛም ተጠቃሚ ሳትሆን መቆየቷን ተናግረዋል።
በኢጋድ ቀጣና አቀፍ የነፃ ቪዛ አለመኖር፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት፣ የሰላምና ፀጥታና ጉዳይ እንዲሁም የመሰረተ ልማት መጓደል ለዘርፉ ፈተና መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በቱሪዝም ልማት ኢትዮጵያ በአዲስ ምዕራፍ በልዩ ትኩረት እየሰራች መሆኑን ገልጸው በዚህም የቱሪስት መዳረሻነቷ እያደገ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም የቀጣናው አገራት ያላቸውን ተሞክሮ መጋራትና ድንበር ተሻጋሪ ቱሪዝም ልማት ላይ በትብብር በመስራት በጋራ ማልማትና ተያይዞ ማደግ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።
የቱሪዝም ፍኖተ ካርታውም ቀጣናዊ መሻታችንን ዕውን ለማድረግ አጋዥ በመሆኑ ለገቢራዊነቱ በቁርጠኝነት መስራት አለብን ያሉት ሚኒስትሯ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።