ኢትዮጵያ በመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ከራሷም ባለፈ የአፍሪካን ጥቅሞች የሚያስከብር ተሳትፎ ለማድረግ ተዘጋጅታለች - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ከራሷም ባለፈ የአፍሪካን ጥቅሞች የሚያስከብር ተሳትፎ ለማድረግ ተዘጋጅታለች - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ፤ መስከረም 9/2017(ኢዜአ):- ኢትዮጵያ በ79ኛው የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ከራሷ ባለፈ የአፍሪካን ጥቅሞች የሚያስከብር ተሳትፎ ለማድረግ መዘጋጀቷን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው፤ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ፣ በአፍሪካ ቀንድ ጂኦ ፖለቲካ ወቅታዊ ሁኔታ እንዲሁም በኢኮኖሚና ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ዙሪያ በማተኮር ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
አምባሳደር ነብያት በመግለጫቸው 79ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ "ማንንም ወደ ኋላ አለማስቀረት ለአሁኑና ለመጭው ትውልድ ሰላም ዘላቂ ልማትና ሰብዓዊ ክብር በጋራ መሥራት" በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄድ መሆኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያም ከመስከረም 14 እስከ 20 ቀን 2017 ዓ.ም በሚካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ ሀገራዊና አህጉራዊ ጥቅሞችን የሚያስከብሩ ሃሳቦችን ይዛ ለመቅረብ ተዘጋጅታለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ በመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጎባኤዎች ሁሉ ተሳትፎ ማድረጓን አስታውሰው ዘንድሮም በጠንካራ ተሳትፎዋ ትቀጥላለች ሲሉ ተናግረዋል።
በዘንድሮው ጠቅላላ ጉባኤ የተመድ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ያመነጩትና ከ140 በላይ ሀገራት መሪዎች በሚሳተፉበት "Summit of the Future" ጉባኤ ላይም ተሳታፊ ትሆናለች ብለዋል፡፡
ይሄ ጉባኤ የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲን ሪፎርም በማድረግ በትውልድ አንድ ጊዜ ሊከሰት የሚችል አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከዋናው ጉባኤ ጎን ለጎን በብሪክስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይም የምትሳተፍ ሲሆን ከአትሚስ ሰራዊት አዋጭ ሀገራት ጋር የጎንዮሽ ውይይት እንደምታደርግም ጠቁመዋል።
የአፍሪካ ቀንድ ጂኦ ፖለቲካን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያም ቀጣናውን የትርምስ አውድማ ለማድረግ የሚደረገው እንቅስቃሴ መቆም አንዳለበት አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቅድሚያ ለጎረቤት ሀገራት መሆኑን ገልጸው፣ የጎረቤት ሀገራት ሰላም የተሳለጠ እንዲሆን ኢትዮጵያ አበክራ ትሰራለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ ማናቸውም ችግሮች በሰከነ ውይይት እንዲፈቱ ጽኑ አቋም እንዳላት አንስተው የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የትርምስ ማእከል ለማድረግ የሚደረግ እንቅስቃሴ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲም ዜጎች ሰብዓዊ ክብራቸው ተጠብቆ መስራት እንዲችሉ የተደረገ መሆኑን አንስተው ዜጎች በደላሎች እየተታለሉ ወደ ማይናማርና ታይላንድ እየተጓዙ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም በህገ ወጥ መንገድ የወጡ ዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ በጃፓንና ህንድ የሚገኙ የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች በቅርበት እየሰሩ ነው ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በህገ ወጥ ደላሎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው ዜጎች ችግርና እንግልት እንዳይደርስባቸው በህጋዊ መንገድ ብቻ ሊጓዙ እንደሚገባ አሳስበዋል።