ቀጥታ፡

የምክክር ሂደቱን በአካታችነት እና አሳታፊነት ማጎልበት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሀላፊነት ነው - ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 9/2017(ኢዜአ):- የምክክር ሂደቱን በአካታችነት እና አሳታፊነት ማጎልበት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ሀላፊነት ሊሆን እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ አስገነዘቡ፡፡

የአገው ለፍትሕ እና ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ ሞቻ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ እና ገዳ ስርዓት ለኦሮሞ ነፃነት ፓርቲ ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡

ሶስቱ ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም ከኮሚሽኑ ጋር አብሮ ከመስራት ራሳቸውን አግልለው የነበሩ መሆናቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

ፓርቲዎቹ ስምምነቱን በተፈራረሙበት ወቅት ከኮሚሽኑ ጋር በጋራ በመስራት የምክክሩን ሂደት ለማገዝ ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸውም ተጠቅሷል፡፡

በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ላይ መሳተፋቸው አስፈላጊ መሆኑን በማመን በሂደቱ ትርጉም ባለው ሁኔታ ለመሳተፍ እንደተዘጋጁም አስታውቀዋል፡፡

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ የኮሚሽኑን አበይት ተግባራት ለፓርቲዎቹ ተወካዮች ማስረዳታቸውም ተመላክቷል፡፡

የምክክር ሂደቱን በአካታችነት እና አሳታፊነት ማጎልበት የሁሉም ባለድርሻ አካል ሀላፊነት ሊሆን እንደሚገባው ዋና ኮሚሽነሩ አስገንዝበዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በኮሚሽኑ ላይ ጥያቄ ኖሯቸው በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ከመሳተፍ ታቅበው የነበሩ አራት የፖለቲካ ፓርቲ ድርጅቶች ማለትም (የአፋር ሕዝቦች ፓርቲ፣ የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር እና የወላይታ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር) ከኮሚሽኑ ጋር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም በምክክሩ እየተሳተፉ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡

በዚህ አጋጣሚ ኮሚሽኑ በሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ላይ ከመሳተፍ ታቅበው የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶች የሂደቱ አካል እንዲሆኑ ጥሪ ማቅረባቸው ተመላክቷል፡፡

ለሚነሱ ጥያቄዎች ውይይቶችን በማድረግ የጋራ መንገድን በማበጀት አብሮ ለመስራት በሩ ክፍት እንደሆነም ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም