የመስከረም ድምቀቶች

መስከረም ዝም ብሎ ወር ብቻ አይደለም። መስከረም ለኢትዮጵያ ውበቷ፣ ቀለሟ፣ ትዕምርቷ፣ የባህር ሃሳቧ መባቻ ነው። መስከረም በባህሉ፣ በትውፊቱ፣ በኪነ እና ስነ-ቃሉ ልዩ ሥፍራ ይሰጠዋል።

እንደ መስከረም ክብር፣ ሞገስ እና ፀጋ የተቸረው የትኛው ወር ይሆን? ሀገሬው ለቆንጆ ልጁ ስም ሲያወጣ ‘መስከረም’ እንጂ በሌላ ወር ሰይሞ አያውቅም። በኢትዮጵያ ምድር መስከረም ለሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን ለእንስሳት እና አዕዋፋት ራሱ ልዩ ጊዜ ነው።

'አገር፣ ቀለም፣ ዘመን' እንደሸማው ድርና ማግ ከሚሆኑባቸው ወራት አንዱ መስከረም ነው። መስከረም አገርኛ አለባበስ፣ አገርኛ ዝማሬ፣ አገርኛ ጨዋታ፣ አገርኛ ትውፊትና ቀለም በተግባር ይታይበታል። መስከረም ሁለንተናዊ ውበቱ ድንቅ ነው፤ ትዕምርቱም ጉልህ ነው። መስከረም የብዙ ድምቀቶች መታያ ወር ነው።

ዘመን መለወጫ

መስከረም 1 ቀን ‘ርዕሰ ዓውደ- ዓመት’ ይሰኛል። የባህር ሐሳብ ሊቃውንት መስከረም ለምን የዘመን መለወጫ እንደሆነ ሲያትቱ “ብርሃናት /ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት/ የዓመት ዑደታቸውን በጳጉሜ ወር ጨርሰው በመስከረም ወር ስለሚጀምሩ ነው” ይላሉ።

’አበባዬ ሆይ፤ አበባዬ ሆይ’ የሚሉ ሕፃናት ተስፋና ምኞታቸውን በወረቀት ያቀልማሉ፤ የአበባ ስዕላት ይዘው በየደጃፉ ይሯሯጣሉ፤ የ’ዕደጉ’ ምርቃት ያገኛሉ፤ በደስታ ይፈነድቃሉ። በዚህ ድባብ ነው እንግዲህ መስከረም የግዑዛንም የሕይወታውያንም የነፃነት፣ የተስፋና የፍቅር ወርኅ ተደርጎ የሚናፈቀው።

በመስከረም ምድር በዕንቁጣጣሽ ትፈካለች፤ በአበቦች ታጌጣለች፤ ውኆች ይጠራሉ። ሰማዩም የክብረ-ሰማይ ብርሃኑን ያጎላል። ጥቁር ደመና ጋቢ ይገፈፋል፤ ክዋክብት እንደፈንዲሻ በዲበ-ሰማይ ይደምቃሉ። ዕጽዋትና አዝዕርት እንቡጦች ይፈነዳሉ። የመብረቅ ነጎድጓድ ተወግዶ የሰላምና የሲሳይ ዝናብ ይዘንባል።

በ’ዕንቁጣጣሽ’ ምድር ብቻ አይደለችም የምትዋበው። መስከረም ለሰው ልጆችም በተለይም ለወጣቶች የፍቅር፣ የእሸት እና የአበባ ወር ነው። የሰላም፣ የንጹህ አየር፣ የጤና ድባብ ያረብባል። የጋመ በቆሎ እሸት ጥብስ፤ ቅቤ ልውስ፤ ቅቤ በረካ ይናፈቃል።

የተጠፋፋ ዘመድ አዝማድ ይገናኛል። ‘ሰኔ መጣና ነጣጠለን’ ብለው ወርኃ ሰኔን የረገሙ ተማሪዎች ተናፋቂያቸውን ያገኛሉና ‘መስከረም ለምለም’ ብለው ያሞካሹታል። የገበሬው የሰብል ቡቃያ ያብባል፤ እሸት ያሽታል። ጉዝጓዝ ሣር፣ ትኩስ ቡና ይሽታል።

ደመራ ወመስቀል

ደመራ መጨመር፣ መሰብሰብ፣ መከመር መሆኑን ሊቃውንት ይገልጻሉ፡፡ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም በመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው ደመራ የሚለውን ቃል ደመረ ከሚለው የግእዝ ቃል የወጣ መሆኑን ያስነብባሉ፡፡ የበዓለ መስቀል ዋዜማ እንጨቶች የሚደመሩበት ስለመሆኑም ያስረዳሉ፡፡

መስቀል በእርሱ ላይ የተሰቀለውን ክርስቶስን ያሳስባል፡፡ ሰውና ፈጣሪን ለዘመናት ለይቶአቸው የነበረው የጠብ ግድግዳ የተናደበትና ሞት ድል የሆነበት የፍቅር ዓርማ መሆኑን የሀይማኖት አባቶች ይገልጻሉ፡፡

ንግሥት ዕሌኒ መስከረም 16 ቀን ደመራ ደምራ በጢስ ምልክት ተመርታ መስቀሉን ከተቀበረበት ለማውጣት ቁፋሮ ያስጀመረችበትን ቀን ምክንያት በማድረግም የመስቀል ደመራ በዓል ይከበራል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያንም ለመስቀል ችቦ እያበሩ በዓሉን በሆታ በእልልታ በስብሐተ እግዚአብሔር ያከብሩታል፡፡

መስከረም 16 እና 17 ቀን የሚከበረው የደመራ መስቀል በዓል ከሃይማኖታዊ አስተምህሮው ባለፈ ባህላዊ ትውፊትነቱ የጎላ በመሆኑ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ይናፈቃል።

ደመራና መስቀል የአንድነት፣ የፍቅር፣ የይቅርታ፣ አብሮነት፣ የምስጋና፣ የተስፋ… እሴቶች የሚገለጹበት ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ክብረ-በዓል ነው።

የኢትዮጵያ የመስቀል በዓል አከባበር በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ የትምህርት እና ባህል ተቋም መዝገብ ውስጥ በዓለም ቅርስነት ከተመዘገቡ የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል አንዱ ነው፡፡

መስቀል በአንዳንድ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ርዕሰ ዓውደ-ዓመት ይመስላል። በደቡብ ኢትዮጵያ መስቀል ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባህላዊ ጎኑ ይጎላል። መስቀልን ከሁሉም በዓላት የበለጠ ይናፍቁታል።

የተራራቁ ቤተሰቦች የሚገናኙበት የፍቅር፣ የደስታና የእርቅ በዓል ነው መስቀል። በጋሞ ብሔረሰብ ባህል ለሰው ብቻ ሳይሆን ለእንስሳቱም ልዩ መኖ እንደሚቀርብላቸው ይነገራል።

መስቀል በጉራጌዎች ዘንድ እንደ አውራው በዓል ይቆጠራል። ለመስቀል ዓመቱን ሙሉ ዝግጅት ይደረጋል። አባወራው ሰንጋ ለመግዛት፣ እማወራ ማጣፈጫውን ለማዘጋጀት፣ ወጣቶች ደመራና ደቦት ለማዘጋጀት፣ ልጆች ምርቃት ለመቀበል የየራሳቸውን ይዘጋጃሉ። ቤተሰብ ወዳጅ ዘመድ የሚጠያየቅበት፣ ጥላቻና ቂም በፍቅርና በይቅርታ የሚታደስበት ነው።

የመስቀል በዓል በሁሉም የኢትዮጵያ አከባቢዎች በልዩ ድምቀት ከሚከበሩት በዓላት መካከል አንዱ ሲሆን እንደየአከባቢዎቹ ባህልና ትውፊት መሠረትም በተለያዩ ኃይማኖታዊና ባህላዊ ሁነቶችም ይከበራል፡፡

መስቀል የወል ክብረ በዓል ነው። የመስቀል ዕለት (መስከረም 17) በግ ይታረዳል። እህል ውሃ ቀርቦ የመንደሩ ሰው በጋራ ሲጫወት ይውላል፤ በሕብረት ይበላል።

ኢሬቻ

ኢሬቻ ከመስከረም ደማቅ መልኮች አንዱ ነው። የኦሮሞ ህዝብ በአንድነት የሚያከብረው ልዩና የማንነቱ መገለጫ የሆነው ኢሬቻ የምስጋና፣ የሰላምና የወንድማማችነት ምልክት ነው፡፡

በኦሮሞ ሕዝብ ባህል ዘንድ ኢሬቻ የሚከበረው ዝናብን፣ ሰላምን፣ ምርት እና የትውልድን ቀጣይነት የሚሰጥ ፈጣሪ በመሆኑ ጤናንና በረከትን የሚችረው እሱ 'ዋቃ' ወይም ፈጣሪ በመሆኑ ምስጋና ለማቅረብ ነው።

የገዳ ስርዓት አንዱ አካል የሆነው ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ በረጅም ጊዜ የሕይወት ውጣ ውረድ ፈጣሪውን የሚያመሰግንብት ባህል፣ ማንነት፣ ስርዓትና ልምድ ነው።

በዓመት ሁለቴ በሚከበረው ኢሬቻ በዓል በአባገዳዎች መሪነት የኦሮሞ ሕዝብ ፈጣሪን የማመስገኛና መማጸኛ ነው።

የተራራ ኢሬቻ (ኢሬቻ ቱሉ) የሚከበረው የበጋው ወራት አልፎ የበልግ ዝናብ በሚጠበቅበት ወቅት ነው። በዚህም ፈጣሪ ''እርጥበት አትንፈገን፣ ወቅቶች ጊዜያቸውን ጠብቀው ይምጡ፣ የዝናብ ንፋስ ስጠን'' በማለት ይለምናሉ።

የመልካ (የውኃ ዳርቻ) ኢሬቻ የሚከበረው በመስከረም ወር አጋማሽ፣ ከደመራ ወይም ከመስቀል በኋላ ባለው ቅዳሜና እሁድ ነው። ይህም በሆራ ፊንፊኔና በሆራ አር ሰዲ ይከበራል። በዚህም የክረምት ወራት የዝናብ፣ የደመናና፣ የጭቃና የረግረግ ወቅት አልፎ ለፈካው ወራት በመብቃቱ ምስጋና የሚያቀርብበት ነው።

ኢሬቻ ለሰላምና ለእርቅ ትልቅ ስፍራ የሚሰጥ በዓል እንደሆነም ይታመናል። በዕለቱ ሰላም የአምላክ ስጦታ መሆኑ ይነገራል፤ ሰላም ከሁሉም ሀብት በላይ መሆኑም ይገለጻል።

በዝናባማው ክረምት በጅረቶችና ወንዞች መሙላት ምክንያት ተራርቀው የነበሩ ቤተ ዘመዶች በባአሉ መከበሪያ ቦታ በባህል ልብሳቸው ድምቀው ይገናኛሉ፤ ይጠያየቃሉ።

ኢሬቻ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የሰላምና የአብሮነት ምልክት በዓል ነው፡፡

በኦሮሞ ሕዝብ ባህላዊ አለባበሱን በማጌጥ ወደ ክብረ-በዓሉ የሚያመሩ ኢሬቻ አክባሪዎች እርጥብ ሳር እና አደይ አበባን ይይዛሉ።

የኢሬቻ በዓል ሲከበር ከሚከወኑ ሥርዓቶች መካከል ሴቶች ሲቄ፣ እርጥብ ሣር እንዲሁም ጮጮ ይዘው ከፊት ሲመሩ አባ ገዳዎች ደግሞ ቦኩ፣ አለንጌ እና ሌሎችንም በበዓሉ ሥርዓት የሚፈቀዱትን ሁሉ በመያዝ ወደ ሥርዓቱ አከባበር ያመራሉ።

ጊፋታ

ጊፋታ በወላይታ ህዝብ ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ታላቅ በዓል ሲሆን ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ የአሮጌው ዓመት ማብቅያና የአዲሱ ዓመት መጀመሪያ የመሸጋገሪያ በዓል ነው፡፡

ጊፋታ ማለት ባይራ (ታላቅ)፣ መጀመሪያ እንደ ማለት ሲሆን በሌላ በኩል ጊፋታ ማለት መሻገር ማለት ነው፡፡ ይህም ከአሮጌ ወደ አዲስ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን መሻገር የሚለውን ይገልጻል፡፡

ጊፋታ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ አእዋፋትና የቤት እንስሳትም ጭምር በጋራ የሚያከብሩት በዓል ነው ተብሎ ይታመናል፡፡

የወላይታ ብሔርሰብ የራሱ የሆነ የዘመን መቁጠሪያ አለው፡፡ በወላይታ የዘመን አቆጣጠር ጊፋታ የዓመቱ የመጀመሪያ ወር ስያሜ ነው፡፡ በበዓሉ “Gifaata Gazzee Abuuna Gaylle” ተብሎ ይዘፈናል፡፡ ይህም የበዓሉን ታላቅነት ለመግለጽ ስለመሆኑ ይነገራል፡፡

ጊፋታ መቃረቡ ከሚገለጽበት መንገድ አንዱ የጉልያ ሥርዓት ይጠቀሳል፡፡ ይሄም በአካባቢው ያሉ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 30 የሚደርሱ ወጣቶች የጉልያ ሥነ ሥርዓት ያከናወናሉ፡፡ ጉልያ ማለት ወጣቶቹ ለደመራ የሚሆን እንጨት የሚለቅሙበትና የሚያዘጋጁበት ወቅት ነው፡፡

ጊፋታ ከመከበሩ ቀደም ብሎ አካባቢን ማፅዳት፣ ቤት ማደስና የዕርቅ ሥራ ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው መካከል ሲሆኑ በጊፋታ ለበዓሉ ድምቀት የሚውል ቅቤ፣ ሠንጋ በሬ፣ አልባሳት፣ ጌጣ ጌጦች፣ የስፌት፣ የሽክላ፣ የብረታ ብረት ምርቶችና ሌሎች ግባቶች የበዓሉ ድምቀት ናቸው፡፡

ግፋታ ሲሸኝ ጥቅምት በገባ በመጀመሪያው ሳምንት ማክሰኞ ሆኖ የሽኝት በሬ ታርዶ ከተበላ በኋላ ቶክ ጤላ የተባለውን ምሽት በችቦ ያባርራሉ፡፡ ዜማ በተቀላቀለበት ጩኸት ችቦ ይዘው ‹‹ኦሎ ጎሮ ባ! ሳሮ ባዳ ሳሮ ያ!›› ይላሉ፡፡ ትርጓሜውም ጊፋታ በሰላም ሄደሽ በሰላም ነይ! ማለት ነው፡፡

ዮ…ማስቃላ

በጋሞዎች ዘንድ በየዓመቱ በጉጉት የሚጠበቀው «ዮ ማስቃላ» የዘመን መለወጫ በዓል በመስከረም ወር አጋማሽ ላይ ቅበላው ተከብሮ በዚሁ ወር መጨረሻ «ዮ ማስቃላ» ሽኝት በዓል በድጋሚ በድምቀት ይከበራል።

መስከረም ወር የመጀመሪያው ቀን በጋሞ ዞን ”ሂንግጫ” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ይህም አዲሱን ዓመት ለመቀበል ዝግጅት የሚደረግበት ቀን ነው።

በጋሞዎች ዘንድ ዓመቱን ሙሉ ገንዘብ በመቆጠብ በዓሉን በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ይደረጋል። ወንዶች ለበዓሉ የሚሆን ሠንጋ መግዣ፣ ለልጆች ልብስ እና ጌጣጌጥ ማሟያ፤ እናቶች ደግሞ ለቅቤ፣ ለቅመማቅመም፣ ለባህላዊ ምግቦች እና መጠጦች እህል መግዣ የሚሆን ገንዘብ ያጠራቅማሉ።

በጋሞ ዞን የማስቃላ በዓል ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን ለእንሳስት እና ለአዕዋፋትም ጭምር ነው ተብሎ ይታመናል፤ በዕለቱ ምግብ ከሰው አልፎ ለእንሳስት እና ለአዕዋፍም ይትረፈረፋል። ለከብቶችም የግጦሸ መሬት በየአካባቢው ይከለላል።

በተለያዩ አጋጣሚዎች የተጣሉ ታርቀው፣ የተራራቁ ዘመድ አዝማድ እና ወዳጆች ተሰባስበው በዓሉን በጋራ እንዲያከብሩ ማድረግ የጋሞ ማስቃላ በዓል መገለጫ ነው።

የመጨረሻው የማስቃላ ሽኝት በዓል እንደየአባወራው አቅም በፈቀደ መጠን የሚፈፀም ነው። በዚህ ዕለት ሁሉም ያለ ፆታ ልዩነት በአደባባይ ላይ ወጥተው ያኑረን እስከ ወዲያኛው እንኖራለን እያሉ ይጨፍራሉ።

ከዚህ በኋላ ለመጪው ዓመት በሰላም በጤና ያድርሰን ተባብለው ፈጣሪን በመማፀን ዝግጅቱ ይቋጫል።

ያሆዴ መስቀላ

የክረምቱ ወራት አልፈው መስኩ በልምላሜና በአደይ አበባ ሲያሸበርቅ በሃድያዎች ዘንድ ትልቅ ዝግጅት አለ - ያሆዴ መስቀላ።

“ያሆዴ“ ማለት እንደ ብሔሩ የባህል ሽማግሌዎች ትርጓሜ እንኳን ደስ አላችሁ፤ የሚል የብስራት ትርጉም ያለው ሲሆን ”መስቀላ” ማለት ደግሞ ብርሃን ፈነጠቀ ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ያሆዴ መስቃላ ብርሃን ፈነጠቀ እንኳን ደስ አላችሁ የሚል ትርጉም አለው።

በዓሉ በወርኃ መስከረም 16 የሚከበር ሲሆን ወሩ ብርሃን፣ ብሩህ ተስፋ፣ ሰላም፣ ፍቅር፣ ረድኤት፣ በረከት የሚሞላበት ተምሳሌት ወር ተደርጎ ይቆጠራል።

የሃድያ አባቶች ”ከባለቤቱ የከረመች ነፍስ በያሆዴ መስቀላ ትነግሳለች“ የሚል ብሂል አላቸው። የሃድያ አባቶች እንደ ዘመን መለወጫ የመጀመሪያ ቀን አድርገው በመውሰድ ማንኛውንም ዓይነት ክስተት ከዚያ ጋር አያይዘው እንደሚቆጥሩ ይነገራል።

ከመጋቢት ወር ጀምሮ ለከብቶች የግጦሽ ሳር የሚሆን ቦታ ከልሎ በማስቀመጥ የበዓሉ ቀን ከብቶች ተለቀውበት እንዲጠግቡ ይደረጋል።

ይህም በአዲስ ዓመት መግቢያ እንኳን የሰው ልጅ እንሰሳትም ቢሆኑ መጥገብ እንዳለባቸውና ሆዳቸው ሳይጎድል አዲሱን ዓመት መቀበል እንዳለባቸው በመታመኑ ልዩ ትኩረት ይሰጣቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ዓመቱ የጥጋብ ዘመን እንዲሆን ለመመኘት ነው።

ጋዜ ማስቃላ እና ዮኦ ማስቃላ

የጎፋ ዞን ሕዝቦች የዘመን መለወጫ በዓላቸው ማለትም “የጎፋ ጋዜ ማስቃላ” እና “የአይዳ ዮኦ ማስቃላ”ን ያከብራሉ። የጎፋ እና ኦይዳ ህዝቦች የዘመን መለወጫ የሆኑት እነዚህ በዓላት በየዓመቱ በወርሃ መስከረም ይከበራሉ።

የጎፋ ጋዜ ማስቃላ እና የኦይዳ ዮኦ ማስቃላ በዓል የተጣላ የሚታረቅበት፣ የተራበ ጠግቦ ለፈጣሪው ምስጋና የሚያቀርብበት፣ የታረዘ የሚለብስበት፣ ጥላቻ ተወግዶ ፍቅር የሚሰበክበት፣ ፍቅር፣ ደስታ፣ ተስፋ እንደ አደይ አበባ የሚፈካበትና ሁሉም ያለልዩነት የሚያከብሩበት በዓል እንደሆነ ይታመናል።

መሳላ

መሳላ በከንባታ፣ ጠንባሮና ዶንጋ ብሄረሰቦች ዘንድ በየዓመቱ የሚከበር በዓል ነው። በዓሉ በከምባታ ህዝብ ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ታላቅ የዘመን መለወጫ በዓል ሲሆን የአሮጌው ዓመት ማብቅያና የአዲሱ ዓመት መጀመሪያ የመሸጋገሪያ በዓል ነው፡፡

መሳላ ማለት (ታላቅ)፣ መጀመሪያ እንደ ማለት ሲሆን በዓሉ ከአሮጌ ወደ አዲስ፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን መሻገር የሚለውን ይገልጻል፡፡

ከምባታዎች አስራ አንድ ወራት በስራ ካሳለፉ በኋላ የመጨረሻውን አንድ ወር ለበዓሉ ያውሉታል፡፡

የመጀመሪያዎቹን 15 ቀናት በበዓሉ ዝግጅት፣ ቀሪዎቹን ቀናት ደግሞ በሀሴት፣ በመዝናናት፣ በመጫወት በጋራ ያሳልፋሉ፡፡

ሄቦ

የየም ብሄረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል 'ሄቦ' ይባላል። የሄቦ በዓል በየም ብሄረሰብ ለዓመት ታቅዶና ታስቦበት የሚከበር የብሄረሰቡ ድንቅ ባህላዊ እሴት ያለው በዓል ነው፡፡

ሄቦ ከመስከረም አጋማሽ ጀምሮ በታላቅ ድምቀት የሚከበር ሲሆን ብሔረሰቡ የተለያዩ የበዓል ዝግጅቶችን አዘጋጅቶ ነጭ በቀይ በሆነው ባህላዊ አልባሳቱ ደምቆ በዓሉን ያከብራል።

የበዓሉ የመጀመሪያ ዕለት 'ካማ ኬሳ' ይሰኛል። የዕርቅ ቀን ሲሆን በቤተሰብ ውስጥም ሆነ በዘመድ አዝማድ መካከል የተፈጠረ ቅራኔና የሰነበተ ቂም ካለ በሽማግሌዎች አማካይነት ሰላም ወርዶ እርቅ የሚፈፀምበት ነው።

'ካማ ኬሳ' በዋናነት ቂምና ቁርሾን ይዞ ወደ አዲሱ ዓመት ላለመሻገር ሲባል እንደሚፈጸምም ነው የሚገለጸው።

ቂምና ቁርሾን ይዞ ወደ አዲሱ ዓመት መሻገሩ ለተለያዩ ማህበራዊ ቀውሶች ሊዳርግ እንደሚችልም በብሔረሰቡ አባላት ይታመናል።

ማሽቃሮ

የካፊቾ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል “ማሽቃሮ” በመባል ይታወቃል። የካፊቾ የዘመን ለውጥ የክረምት ወቅትን ተከትሎ ይከበራል።

የካፋ ህዝብ የማሽቃሮ አዲስ ዓመት ከገበሬው የእርሻ ስራ ጋር የተያያዘ ሲሆን መለያውም ከመዝራት፣ ከእድገት እና ከመኸር ዑደት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይነገራል።

የካፋ ንጉስ መቀመጫ በሆነውና በየዓመቱ በዓሉ በሚከበርበት “ቦንጌ ሻንቤቶ” በሚባለው ስፈራ በዓሉ ሲከበር በዞኑ የሚኖሩ ብሔረሰቦችን ባህላዊ እሴቶቻቸውን የሚያሳይ ስነ ስርዓት ያካሂዳሉ።

ኢትዮጵያ የብዙ ሀይማኖታዊና ባህላዊ ሀብቶች መገኛ ነች። በሁሉም ማዕዘኖቿ አያሌ ቱባ ሀብቶችን የተቸረች ህብረ ብሄራዊነት የጎላባት ሀገር ነች። በዚህ ጽሁፍ የተወሰኑትን የመስከረም ድምቀቶች ዳሰስን እንጂ የኢትዮጵያ መገለጫዎች አይነተ ብዙ እሴቶቿም እጹብ ድንቅ ናቸው።

በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች በወርሃ መስከረምም ይሁን በሌላ ወራት የሚከበሩ የህዝቦቿን ሀብቶች አጉልቶ ማሳየት፣ ለማህበረሰባዊ ትስስርና ለአብሮነት መጎልበት መጠቀም ይገባል።

ቸር እንሰንብት

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም