ኢትዮ ቴሌኮም በ2017 በጀት ዓመት አጠቃላይ ገቢውን 163 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ማቀዱን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮ ቴሌኮም በ2017 በጀት ዓመት አጠቃላይ ገቢውን 163 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ማቀዱን አስታወቀ

አዲስ አበባ፤መስከረም 9/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮ ቴሌኮም በ2017 በጀት ዓመት አጠቃላይ ገቢውን 163 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ማቀዱን የኩባንያው ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ገለጹ።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ፤ የኩባንያውን የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በተያዘው ዓመት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025ን ስኬት እውን ለማድረግ የተጀመሩ ቁልፍ ተግባራት ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን ገልጸዋል።
በ2017 በጀት ዓመት ለዲጂታል መሰረተ ልማት ግንባታ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ መመደቡን ጠቅሰው፥ በቴሌኮምና ዲጂታል መሠረተ ልማት ግንባታ ላይ በልዩ ትኩረት ይሰራል ብለዋል።
በ2017 ዓ.ም ኩባንያው አዳዲስ አገልግሎቶችን ይዞ የሚመጣ መሆኑን ጠቅሰው፥ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን የማፋጠን ስራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል ሲሉም ተናግረዋል።
በበጀት አመቱ የ4 ጂ ኔትወርክ ተጣቃሚ ባልሆኑ 500 ከተሞች እንዲሁም በ15 ከተሞች የ5ጂ ኔትወርክ አገልግሎት ተደራሽ የሚደረግ መሆኑንም ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ አጠቃላይ ገቢውን 163 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ለማድረስ መታቀዱን ጠቅሰዋል።
የደንበኞቹን ቁጥርም 83 ሚሊየን ለማድረስ እንዲሁም የቴሌብር ደንበኞችን ወደ 55 ሚሊየን ለማሳደግ ታቅዷል ብለዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ኩባንያው 93 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱ ይታወሳል።