የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ ባለፈ የጥናትና ምርምር ዘርፉንና የማህበረሰብ አገልግሎትን ለማሳደግ እንሰራለን - ኢዜአ አማርኛ
የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ ባለፈ የጥናትና ምርምር ዘርፉንና የማህበረሰብ አገልግሎትን ለማሳደግ እንሰራለን
መቀሌ ፤ መስከረም 09/2017(ኢዜአ)፡- በትምህርት ዘመኑ የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ ባሻገር የጥናትና ምርምር ስራዎችን እና የማህበረሰብ አገልግሎትን ለማሳደግ እንደሚሰሩ የራያና የአክሱም ዩኒቨርሲቲዎች አስታወቁ፡፡
ዩኒቨርሲቲዎቹ በ2017 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ስራውን ለማስጀመር ዝግጅት ማጠናቀቃቸውንም ለኢዜአ ገልፀዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲዎቹ ፕሬዚዳንቶች ለኢዜአ እንደገለፁት፤ የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ ባሻገር የጥናትና ምርምር ስራዎችን እና የማህበረሰብ አገልግሎትን ለማሳደግ በስፋት ይሰራሉ።
የራያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ታደሰ ደጀኔ እንደተናገሩት፤ ዩኒቨርሲቲው በአካባቢው የግብርና ልማት አሰራርን ለማዘመን የሚያስችሉ ተግባራትን ያከናውናል።
ዩኒቨርሲቲው ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችና የልማት ተቋማት ጋር በመተባበር በቲሹ ካልቸር፣ በአፈር ለምነትና በመስኖ ልማት የአካባቢውን ማህበረሰብ እና አርሶ አደር የሚጠቅሙ ፕሮጀክቶችን ለማከናወን እቅድ መያዙን ተናግረዋል፡፡
ከአገር ውስጥና ከውጭ የምርምር ተቋማት ጋር በመተባበርም ችግር ፈቺ የማህበረሰብ ጥናትና ምርምር ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም ፕሬዚዳንቱ አመልክተዋል።
ፕሬዚዳንቱ አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው ለ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን ገልፀዋል።
የተማሪዎች መኝታ፣ መመገቢያ፣ መማሪያ ክፍሎችን የማጽዳትና የማሳደስ እንዲሁም አዲስ ለተገነቡ ክፍሎች የመሰረተ ልማት የማሟላት ስራ መሰራቱን አመልክተዋል።
ነባር ተማሪዎች መስከረም 13 እና 14 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚገቡ ገልጸው፤ በትምህርት ሚኒስቴር የሚመደቡ ከሁለት ሺህ በላይ አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበልም ዝግጅት መደረጉን ጠቁመዋል፡፡
የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ገብረየሱስ ብርሃነ በበኩላቸው፤ በትምህርት ዘመኑ ተግባር ተኮር ትምህርትን በማጠናከር የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማሳደግ፣ የዩኒቨርሲቲና ኢንዱስትሪ ትስስርን ለማጎልበት ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲው ነባር ተማሪዎችን መቀበል መጀመሩን ገልፀው፣ አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉንም ተናግረዋል።
የመምህራንን አቅም የመለየትና የትምህርት ዘመኑን የመተግበሪያ መርሀ ግብር የማዘጋጀት ስራ ተጠናቆ ወደ ተግባር መገባቱንም ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል፡፡
የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የቤተ-ንባብ እና የቤተ-ሙከራ ግብዓቶችን በማሟላት ለትምህርት ዘመኑ ሙሉ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።