በሀዋሳ ከተማ በአንድ ቢሊዮን ብር በጀት የኮሪደር ልማት ሥራ እየተከናወነ ነው

ሀዋሳ፤ መስከረም 9 /2017 (ኢዜአ)፦በሀዋሳ ከተማ በበጀት ዓመቱ በአንድ ቢሊዮን ብር በጀት የኮሪደር ልማት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የአስተዳደሩ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ኃላፊ ኢንጂነር ምህረቱ ገብሬ ለኢዜአ እንዳስታወቁት ሀዋሳ ከተማን ይበልጥ ውብ እና ማራኪ ለማድረግ ለመሠረተ ልማት ግንባታ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

በዚህም ዘንድሮ እየተተገበሩ ካሉ የልማት ሥራዎች መካከል አንዱ በተመረጡ የከተማዋ አካባቢዎች የተጀመረው የመንገድ ኮሪደር ልማት አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

የኮሪደር ልማቱ በአንድ ቢሊዮን ብር ወጪ እንደሚከናወን ገልጸው፣ እስካሁንም ለመነሻ የሚሆነው 354 ሚሊዮን ብር ለዚሁ ሥራ በተከፈተ የባንክ ሒሳብ ውስጥ ገቢ ተደርጓል ብለዋል።

 

የኮሪደር ልማት ሥራው ከሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ ወደተግባር መገባቱንና ሥራውም በመፋጠን ላይ መሆኑን አመልክተዋል።

እንደመምሪያ ሃላፊው ገለጻ የኮሪደር ልማቱ በዋናነት ሰፋፊና ምቹ የእግረኛ መንገድ፣የብስክሌት መጋለቢያ፣የአረንጓዴ ልማት፣ ፋውንቴን፣ መዝናኛ የልጆች መጫወቻ እና የስፖርት ማዘውተሪያዎችን የሚያካትት ነው።

ሥራው በቀንና በማታ በሳምንት ለሰባት ቀናት እንዲከናወን መምሪያው የቅርብ ክትትል በማድረግ ለልማቱ መፋጠን ቁልፍ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም መምሪያ ሃላፊው አስታውቀዋል።

የመጀመሪያው ምዕራፍ አካል የሆኑ የሁለት ተጨማሪ ፕሮጀክቶች ግንባታ በቅርቡ ለማስጀመር አካባቢውን ምቹ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።


 

እንደ ሃላፊው ገለጻ በከተማው ከሳውዝ እስታር እስከ ሻፌታ አደባባይ ድረስ ለሚከናወነው የ3 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ርዝመት ላለው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ኢንጂነሪንግ ኮርፕሬሽን የዲዛይን ሥራው በመጠናቀቅ ላይ ነው።

በቅርቡ የሥራ ተቋራጭ መረጣ ተካሂዶ ወደግንባታ ሥራ እንደሚገባም አስታውቀዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ በከተማዋ ከሻፌታ አደባባይ ወደ ሀይሌ ሪዞርት፣ ከታቦር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ ግሎባል ጋራዥ 5 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የኮሪደር ልማት ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማትም ህብረተሰቡንና የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን በማስተባበር በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ልማቱ እንደሚከናወን ገልጸዋል።

በዚህም 6 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የኮሪደር ልማት ለማከናወን መታቀዱንና የዲዛይን ርክክብ መጠናቀቁን ኢንጂነር ምህረቱ አመልክተዋል።


 

በከተማው የኮሪደር ልማት ሥራውን ተረክቦ እያከናወነ ያለው "ኢንጂነር ተስፋዬ ኮንስትራክሽን ድርጅት" ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ተስፋዬ ፀጋዬ በበኩላቸው፣ 1 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን የኮሪደር ልማት በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ሌት ተቀን እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በፕሮጀክቱ ለ280 ወጣቶች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ጠቅሰው፣ በግንባታ ሂደት ንብረትን ፈጥኖ ካለማንሳት በቀር ያጋጠመ ችግር አለመኖሩን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱን በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ መሰረት አጠናቆ ለማስረከብ ያለእረፍት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተለይ ለከተማዋ የመንገድ ኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ስኬታማነት የከተማዋ ነዋሪዎች፣የንግዱ ማህበረሰብ እና የከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ ለልማቱ መፋጠን አዎንታዊ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

እንደ ኢንጂነር ተስፋዬ ገለፃ የኮሪደር ልማቱ ዘመናዊ መንገድን ያካተተ ከመሆኑ በላይ ዓለም አቀፍ የስማርት ሲቲ ስታንዳርድን በማሟላት የከተማዋን ደረጃ ከፍ ለማድረግ ጠቀሜታው የጎላ ነው።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም