ቀጥታ፡

አፍሪካ ቀንድ ቀጣናን የትርምስ ማዕከል ለማድረግ የሚደረግ እንቅስቃሴ ሊቆም ይገባል- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 9/2017(ኢዜአ)፦ አፍሪካ ቀንድ ቀጣናን የትርምስ ማዕከል ለማድረግ የሚደረግ እንቅስቃሴ ሊቆም እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በኢትዮጵያ ወቅታዊ የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ጉዳዩች ላይ ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

አምባሳደር ነብያት በመግለጫቸው፣ ኢትዮጵያ ቀጣናውን የትርምስ አውድማ ለማድረግ የሚደረገው እንቅስቃሴ ሊቆም ይገባል የሚል ጽኑ እምነት እንዳላት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቅድሚያ ለጎረቤት ሀገራት መሆኑን ገልጸው፣ የጎረቤት ሀገራት ሰላም የተሳለጠ እንዲሆን ኢትዮጵያ አበክራ ትሰራለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሰላምና በመሰረተ ልማት የተሳሰረ ጉርብትና እንዲኖር ንቁ ተሳትፎ እያደረገች መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ችግሮች በሰከነ ውይይት እንዲፈቱ ጽኑ አቋም እንዳላት አንስተው፤ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን የትርምስ አውድማ ለማድረግ የሚስተዋለው እንቅስቃሴ ግን ሊቆም ይገባል ብለዋል።

ችግሮች መስመር እንዲስቱ ለማድረግ የሚሰነዘሩ ሀሳቦች ተገቢነት እንደሌለቸውም ነው ያነሱት፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያ ከመስከረም 14 እስከ መስከረም 20 ቀን 2017 በመሪዎች ደረጃ በሚከናወነው 79ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ በንቃት ለመሳተፍ ቅድመ ዝግጅት ማድረጓን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በተመድ ጠቅላላ ጎባኤ ለ79 ዓመታት በንቃት መሳተፏን የገለጹት አምባሳደር ነብያት፣ በቀጣዩ ጉባኤም የራሳን ብሎም የአፍሪካን ጥቅም በሚያስጠብቁ ጉዳዮች ላይ በንቃት ትሳተፋለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከዋናው ጉባኤ ጎን ለጎን በብሪክስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ በንቃት እንደምትሳተፍም ነው ያነሱት።

በተጨማሪም ከአትሚስ ሰራዊት አዋጭ ሀገራት ጋር የጎንዮሽ ውይይት እንደምታደርግም ገልጸዋል።

ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብሩ ሁለንተናዊ ግንኙነቶች ላይ ለመወያየት ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም