ቀጥታ፡

የኢጋድ አባል ሀገራትን ማዕከል ያደረገ ቀጣናዊ የ10 ዓመት ዘላቂ የቱሪዝም ፍኖተ ካርታ ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፤መስከረም 9/2017(ኢዜአ)፦የኢጋድ አባል ሀገራትን ማዕከል ያደረገው ቀጣናዊ የ10 ዓመት ዘላቂ የቱሪዝም ፍኖተ ካርታ ይፋ ሆኗል።

ፍኖተ ካርታው ይፋ የሆነው የቱሪዝም ሚኒስቴር ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር ከዛሬ ጀምሮ የሚከበረውን የዓለም የቱሪዝም ቀን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀው የቱሪዝም መድረክ ላይ ነው።

የኢጋድ አባል ሀገራትን የተለያዩ የቱሪዝም ዘርፍ ተዋኒያን ያሳተፈ የቱሪዝም ዓውደ ርዕይ መከፈቱ ይታወሳል።

በመድረኩ የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ፣ የቱሪዝም ሚኒስትሯ ናሲሴ ጫሊን ጨምሮ የአባል ሀገራት የቱሪዝም ሚኒስትሮች፣ አጋር ድርጅቶች ተወካዮች እና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ዶክተር ወርቅነህ በዚህ ወቅት እንዳሉት የኢጋድ አባል ሀገራት ዘላቂ የቱሪዝም ፍኖተ ካርታ ከ2024 እስከ 2034 የሚተገበር እና በቀጣናው ቱሪዝም ተወዳዳሪ፣ዘላቂ ሆኖ እንዲቀጥል ማስቻል ነው።

ከትናንት በስትያ ይፋ ያደረገችውን ኢትዮጵያን ጨምሮ አባል ሀገራት የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት እያወጡ መሆኑን ገልፀው፣ ይህም ለዘርፉ እምርታ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

የ10 ዓመቱ ፍኖተ ካርታም ለፖሊሲ አውጭዎች የሚበጅ ብሎም ቀጣናዊ ትስስር የሚያጎለብት ወሳኝ እርምጃ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢጋድ ቀጣና በተፈጥሮ ሀብትና በባህል ብዝሀ ፀጋ የተቸረው መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህን ፀጋ እሴት ጨምረን በትብብር ማልማትና መጠቀም ይገባል ነው ያሉት።

የቀጣናውን ተፈጥሯዊና ባህላዊ ሀብቶች ጠብቀን ለቀጣይ ትውልድ ማሻገር ይገባናል ብለዋል።

በቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት እንዲጎለበትና የህዝብ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ያለውን ፋይዳ በመረዳት፤ለፍኖተ ካርታው ትግበራም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ቱሪዝም በፈተናዎች ውስጥም ሆኖ የወደፊት የቀጣናው ኢኮኖሚ መጎልበት ወሳኝ ፋይዳ እንደሚኖረው ጠቁመው፣ኢጋድ ለቀጣናው ልማትና ሰላም መረጋጋት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የቱሪዝም ሚኒስትሯ ናሲሴ ጫሊ በበኩላቸው አፍሪካ ዕልቆ ቢስ የቱሪዝም መስህቦች ቢኖራትም ቱሪዝም ልማት ላይ በቅጡ ባለመሰራቱ ዘርፉ ያለው የኢኮኖሚ አበርክቶ አናሳ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ኢጋድ ቀጣና አቀፍ የነፃ ቪዛ አለመኖር፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል፣ ሰላምና ፀጥታና መሰል ተግዳሮቶችን በመቅረፍ ዘርፉን ማጎልበት ይገባል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በቱሪዝም ልማት አዲስ ምዕራፍ ላይ መሆኗን ጠቅሰው፣ ባለፉት ዓመታት መሰረተ ልማት ዝርጋታን ጨምሮ በዘርፉ የተከናወኑ ተጨባጭ እምርታዎችን ጠቅሰዋል።

ይህም ኢትዮጵያ የቱሪስት መዳረሻነቷ እያደገ መምጣቱን ገልፀው፣ የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎችም ለተወዳዳሪና ዘላቂ የቱሪዝም እድገት የሚበጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ነገር ግን የቀጣናው ሀገራት ያላቸውን ተሞክሮ መጋራትና ድንበር ተሻጋሪ የቱሪዝም ልማት ላይ በትብብር መስራት እንደሚጠይቅ ገልፀዋል።

በዕለቱ ይፋ የተደረገው የቱሪዝም ፍኖተ ካርታ ቀጣናዊ መሻታችንን ዕውን ለማድረግ አጋዥ መሳሪያ በመሆኑ ለገቢራዊነቱ ቁርጠኝነት ሊኖረን ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም