ባለስልጣኑ ሕብረተሰቡ ፈቃድ የሌላቸውን ሦስት ሕገወጥ የከረሜላ ምርቶች እንዳይጠቀም ማሳሰቢያ ሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
ባለስልጣኑ ሕብረተሰቡ ፈቃድ የሌላቸውን ሦስት ሕገወጥ የከረሜላ ምርቶች እንዳይጠቀም ማሳሰቢያ ሰጠ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 9/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ሕብረተሰቡ ምንጫቸው ያልታወቁና የምርት ፈቃድ የሌላቸውን ሦስት ሕገ-ወጥ የከረሜላ ምርቶችን እንዳይጠቀም አሳሰበ።
ባለስልጣኑ ከሕብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሰረት በነሐሴ ወር በመርካቶ ገበያ ባደረገው የዳሰሳ ሥራ ብሔራዊ አስገዳጅ ገላጭ ጽሑፍ ደረጃ CES 73/2013 ሳያሟሉ ገበያ ላይ የተገኙ ሦስት አይነት የከረሜላ ምርቶችን ይዟል፡፡
እነዚህ ህገወጥ የከረሜላ ምርቶች ማን እንዳመረታቸው፣ የት አገር እንደተመረቱ፣ የአምራቹ አድራሻ ያልታወቀና የምርቱ ባች ቁጥር የሌለው በመሆኑ የሀገሪቱን አስገዳጅ ገላጭ ፅሑፍ ደረጃ የማያሟሉ በመሆናቸው ሕብረተሰቡ እንዳይጠቀማቸው ማሳሰቡን ከባለስልጣኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
ባለስልጣኑ ሕብረተሰቡ መሰል ጤናን የሚጎዱ ሕገ-ወጥ ምርቶች ሲያጋጥሙት በነፃ የስልክ መስመር 8482 ወይም በየአካባቢው ላሉ የጤና ግብዓት ተቆጣጣሪ ተቋማት አልያም ለፖሊስ አካላት ጥቆማ በመስጠት ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪውን አቅርቧል፡፡