ለመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት አከባበር 16 ሺህ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ለማስተባበር ተዘጋጅተዋል- የወጣቶች ማህበር - ኢዜአ አማርኛ
ለመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት አከባበር 16 ሺህ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ለማስተባበር ተዘጋጅተዋል- የወጣቶች ማህበር
አዲስ አበባ፤መስከረም 9/2017(ኢዜአ)፦ለመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት አከባበር 16 ሺህ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ለማስተባበር መዘጋጀታቸውን የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር አስታወቀ።
በመስከረም ወር በደማቅ ስነስርአት ከሚከበሩት የአደባባይ በዓላት መካከል የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት ይጠቀሳሉ።
በእነዚህ በዓላት በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ አገራት ቱሪስቶች፣ የበዓሉ አክባሪዎችና ታዳሚዎች ይሳተፉበታል።
በዚሁ መሰረት ለሚከበሩት የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት አዲስ አበባ እንግዶቿን ተቀብላ ለማስተናገድ ከወዲሁ ሁለንተናዊ ዝግጅት በማድረግ ላይ ትገኛለች።
ለበዓላቱ ሰላማዊ የአከባበር ሂደት ለአቀባበልና መስተንግዶ በርካታ የመዲናዋ ወጣቶች መዘጋጀታቸውን የአዲስ አበባ ወጣቶች ማኅበር አስታውቋል።
የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ ይሁነኝ መሀመድ፤ የኢትዮጵያ መገለጫና የዓለም ሃብት የሆኑትን የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት እሴታቸው ተጠብቆ በደማቅ ስነስርአት እንዲከበሩ የበኩላችነን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ብሏል።
በሁነቱ ላይ እንግዶችን ለመቀበል፣ ለማስተባበርና ለማስተናገድ 16 ሺህ የማህበሩ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግሯል።
ከማህበሩ አባላት መካከል ወጣት ዮሴፍ አደል እና ብርቱካን በቀለ፤ ለበዓላቱ ስኬታማ አከባበርና ሰላማዊ ሂደት የበኩላችንን አስተዋጽኦ ለማበርከት ተዘጋጅተናል ሲሉ ተናግረዋል።
የሰላም፣ የአንድነት፣ የፍቅርና የአብሮነት ማሳያ የሆነው ኢሬቻ በዓል እና ከሀይማኖታዊ በዓልነቱ በተጨማሪ በማህበረሰባዊ በዓልነቱ የሚታወቀው የመስቀል ደመራ በዓል ኢትዮጵያ በዓለም የማይዳሰስ ቅርስነት ካስመዘገበቻቸው ቅርሶች መካከል መሆናቸው ይታወቃል።