ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስና የፀጥታና ደኅንነት አካላት ጋር ሀገራዊ የፀጥታ ሁኔታዎችን ገመገሙ

አዲስ አበባ፤መስከረም 9/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከፀጥታና ደኅንነት አካላት ጋር ሀገራዊ የፀጥታ ሁኔታዎች ግምገማ አካሄደ።

በጳጉሜን ቀናት ሲካሄዱ የነበሩ ፕሮግራሞች፣የ2017 ዓ.ም የዘመን መለወጫና የመውሊድ በዓላት አዲስ አበባ ከተማ ጨምሮ በሁሉም የሀገሪቷ አካባቢዎች ያለ ምንም የፀጥታ ችግር በሰላም ተከብረው ማለፋቸውን የፀጥታ አካላት ባቀረቡት የአፈፃፀም ሪፖርት ላይ ተመላክቷል።

በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች ሕግን ለማስከበር እየተደረገ ያለው የተቀናጀና ጠንካራ ኦፕሬሽን ተጠናክሮ መቀጠሉ ተጠቁሟል።

ተልዕኮ ይዘው ወደ አዲስ አበባ ከተማና ሌሎች የሀገሪቷ ከተሞች ሰርገው ለመግባት ሲሞክሩ የነበሩ የሸኔና የፅንፈኛው ፋኖ የሽብር ቡድን አባላትን በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ በግምገማው ወቅት ተገልጿል።


 

ከዚህም ባለፈ በአዲስ አበባ ከተማ ሞባይል ንጥቂያና ተደራጅተው የተለያዩ ወንጀሎችን በመፈፀም ሕብረተሰቡን የሚያስመርሩ ቡድኖችና ግለሰቦችም በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራው እየተደረገባቸው መሆኑም ተነስቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ የፀጥታ ሁኔታ አሁን ላይ በአስተማማኝ ሰላምና ደኅንነት ላይ እንዳለ የፀጥታና ደኅንነት አካላት ባደረጉት ግምግማ ገልጸዋል።

በቀጣይም በአደባባይ በከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር የሚከበሩ የመስቀልና የኢሬቻ በዓላት ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲጠናቀቁ ጠንካራ ዝግጅት እንደተደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ሕብረተሰቡ እስከ አሁን ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር ላደረገው ድጋፍ ምስጋና የቀረበ ሲሆን ይህንኑ ትብብሩን ይበልጥ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ መቅረቡን ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም