ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከኩባ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት በአዲስ የትብብር አማራጮች ይበልጥ ለማጠናከር ትሰራለች - አምባሳደር አየለ ሊሬ

አዲስ አበባ፤መስከረም 9/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከኩባ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት በአዲስ የትብብር አማራጮች ይበልጥ ለማጎልበት እንደምትሰራ በኩባ የኢትዮጵያ አምባሳደር አየለ ሊሬ ገለጹ።

አምባሳደር አየለ ሊሬ የሹመት ደብዳቤያቸውን ለኩባ ምክትል ፕሬዝዳንት ሳልቫዶር አንቶኒዮ ቫልዴዝ ሜሳ አቅርበዋል።

አምባሳደሩ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለኩባ ፕሬዝዳንት ሚጉዌል ዲያዝ-ካኔል ቤርሙዴዝ የተላከ መልዕክትንም አድርሰዋል።

ኢትዮጵያና ኩባ ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ትብብርና ፍሬያማ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላቸው አምባሳደር አየለ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ከኩባ ጋር ያላትን ታሪካዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከርና በአዳዲስ የትብብር መስኮች ወዳጅነቷን ለማጎልበት እንደምትሰራ አመልክተዋል።

የኩባ ምክትል ፕሬዝዳንት ሳልቫዶር አንቶኒዮ ቫልዴዝ ሜሳ ኢትዮጵያን እ.አ.አ በ2023 መጎበኘታቸውንና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጋር መወያየታቸውን አስታውሰዋል።


 

ምክትል ፕሬዝዳንቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሰላምታና መልካም ምኞት መግለጫቸውን አስተላልፈዋል።

ኩባ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከርና አገራቱ በኢንቨስትመንትና ቴክኖሎጂ መስኮች የተፈራረሟቸው የትብብር ስምምነቶች ተፈጻሚ እንዲሆኑ በቁርጠኝነት ትሰራለች ብለዋል።

ቫልዴዝ ሜሳ ኢትዮጵያ ለኩባ በባለብዙወገን የትብብር መድረኮች እያደረገች ላለው ያልተቋረጠ ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያና ኩባ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዲጠናከር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም ነው የገለጹት።

አምባሳደር አየለ ሊሬ በኩባው ብሔራዊ ጀግና ሆዜ ማርቲ ሐውልት ስር የመታሰቢያ አበባ ጉንጉን ማስቀመጣቸውን ኢዜአ በኩባ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያና ኩባ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እ.አ.አ በ1975 መጀመራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም