ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ የተገነቡ የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎች ለቀጣናው ሀገራት በጥሩ ማሳያነት የሚጠቀሱ ናቸው- የኢጋድ አባል አገራት የቱሪዝም ኃላፊዎች

አዲስ አበባ፤መስከረም 8/2017(ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ የተገነቡ የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎች ለቀጣናው ሀገራት በጥሩ ማሳያነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) አባል አገራት የቱሪዝም ዘርፍ የስራ ኃላፊዎች ገለጹ።

የኢጋድ አባል ሀገራት የቱሪዝም የስራ ኃላፊዎች በአዲስ አበባ ዓድዋ ድል መታሰቢያ፣ እንጦጦ ፓርክ እና በሳይንስ ሙዚየም ጉብኝት አድርገዋል።

በዓለም አቀፍ የቱሪዝም ቀን የተዘጋጀው ጉብኝት በቱሪዝም ሚኒስቴር፣ በኢጋድ እና በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ትብብር የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።

የደቡብ ሱዳን የዱር እንስሳት ጥበቃ እና ቱሪዝም ሚኒስትር ራዚክ ዛካሪያ ሀሰን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና መንግስታቸው በአጭር ጊዜ የሚያኮራ የመስህብ ልማት ስራ ሰርተዋል ብለዋል።


 

የጎበኟቸው የቱሪዝም መስህብ ስፍራዎችም የአፍሪካዊያን መዲና ለሆነችው አዲስ አበባ ከነበሯት ቀደምት ቅርሶች ባሻገር ለዘርፉ ልማት አቅም የሚሆኑ አስደናቂ የልማት ስራዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ የተከናወኑ የቱሪዝምና የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎችም ከተማዋን ውብ ገጽታ ያላበሱና ለቀጣናው ሀገራት በጥሩ ማሳያነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የዑጋንዳ የቱሪዝም የዱር እንስሳትና ጥንታዊ ቅርሶች ሚኒስትር ዴኤታ ባሂንዱካ ማርቲን ሙጋራ፤ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ኢትዮጵያዊያን ለነፃነታቸው የከፈሉትን ውድ ዋጋ የሚያስታውስ ድንቅ የታሪክ ማስታወሻና ቋሚ ቅርስ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ይፋ ማድረጓም ከዘርፉ ያላትን ዕምቅ አቅም ለመጠቀም የሚያግዝና እድገቷንም የሚያፋጥን ነው ብለዋል።

በቱሪዝም ሚኒስትር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አለማየሁ ጌታቸው፤ ጉብኝቱ የቀጣውን ሀገራት የቱሪዝም ልማት ትብብር ለማጠናከር ዓለማ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በጉብኝቱም ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) አባል ሀገራት የተውጣቱ የስራ ኃላፊዎችና ሙያተኞች መሳተፋቸውን ተናግረዋል።

የቀጣናው ሀገራትም በቱሪዝም መስክ ያላቸው አቅም ተጠቅመው ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን እንዲያሳልጡ ለማስቻል ልምድና ተሞክሮ የተለዋወጡበት አጋጣሚ መሆኑንም አንስተዋል።

በእለቱም የኢጋድ የስራ ሃላፊዎችና የቱሪዝም ሚኒስትሮች፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የስራ ኃላፊዎችና ሌሎችም የዘርፉ ባለሙያዎች በተገኙበት እ.አ.አ ከ2024 እስከ 2034 የሚቆየው የምስራቅ አፍሪካ የቱሪዝም ፍኖተ ካርታ ላይ ውይይት ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም