ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች የልሕቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 8/2017(ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች የልሕቀት ማዕከል ለመሆን እየሰራ መሆኑን የዩኒቨርስቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ተመስገን ወንድሙ (ዶ/ር) ገለጹ። 

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩንቨርሲቲ ላለፉት ሰባት ዓመታት ትኩረቱን በሳይንስና ቴክኖሎጂ መስኮች ላይ አድርጎ ተማሪዎችን እያሰለጠነ ይገኛል።

ተቋሙ በዋናነት በሳይንስ፣ በኢንጂነሪንግና በቴክኖሎጂ ዘርፎች አገሪቱ የምትፈልገው የሰው ኃይል ለማፍራትና እድገቱን ለማፋጠን እየሰራ መሆኑን ገልጿል። 

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ተመስገን ወንድሙ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ዩንቨርሲቲው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፉን ለማገዝ እየሰራ ነው። 

በዘርፉ ተማሪዎችን ተቀብሎ ከማሰልጠን ባሻገር የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስና የሮቦት ቴክኖሎጂዎችን ጨምሮ በስምንት መስኮች ላይ የልህቀት ማዕከል እየገነባ መሆኑን ገልፀዋል። 

የልሕቀት ማዕከሉ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በሮቦቲክ፣ በናኖ ቴክኖሎጂ፣ በማዕድን፣ በባዮ ቴክኖሎጂ፣ በኮንስትራክሽን ጥራት፣ በኒውክለር ሳይንስ ዘርፎች ላይ እንደሚሰራም ነው የተናገሩት።  

የኒቨርሲቲው በዘርፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ያለ ቦታ ሊያሰጠውና አቅሙን ለማሳደግ በሚያስችለው  የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ በተለየ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። 

በተለይም የኢትዮጵያን እድገት ሊያፋጥኑ የሚችሉ የዘርፉ ቴክኖሎጂዎችን በሚያሳድጉ መስኮች ላይ በልዩ ሁኔታ እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም