ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ ተገለጸ

 ባህር ዳር ፤ መስከረም  8/2017(ኢዜአ)፡-  በአማራ ክልል በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ  ችግር ላጋጠማቸው  ወገኖች ከሰብዓዊ እርዳታ  በተጓዳኝ በዘላቂነት ለማቋቋም የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ  የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን ገለጸ።

በሰሜን ጎንደር ዞን ጠለምት ወረዳ በአብ እና ግልቤ ቀበሌዎች በመሬት መንሸራተት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የአልባሳት ድጋፍ ርክክብ ተካሄዷል።

ድጋፉን ያደረገው የአማራ ልማት ማህበር (አልማ) ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ጋር በመተባበር መሆኑን በርክክቡ ወቅት ተገልጿል። 

በባህር ዳር ከተማ ድጋፉን የተረከቡት የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ ሰርክአዲስ አታሌ እንዳሉት፤ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግር  የተጎዱ ወገኖች የዕለት ደራሽ ድጋፍና ዘላቂ መፍትሄ ይሻሉ።


 

በቅርቡ በሰሜን ጎንደር ዞን በተከሰተው የመሬት መንሸራተት ምክንያት የዕለት ደራሽ ድጋፍ ለማድረስ መንግስትና አጋር አካላት ርብርብ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ህብረተሰቡ ለከፋ ጉዳት ሳይዳረግ መታደግ መቻሉን ጠቅሰው፤ ይህ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።

በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ችግር ተፈናቅለው በክልሉ በመጠለያ ካምፕና በህብረተሰቡ ውስጥ የሚገኙ ወገኖች ከሰብዓዊ ድጋፍ በተጓዳኝ  በዘላቂነት ለማቋቋም የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ  ገልጸዋል።

ለዚህም የተፈናቀሉትን  ወደ ቀደመው የመኖሪያ ቀያቸው መልሶ ከማስፈር በተጨማሪ ሌሎቹ ባሉበት አካባቢ መሰረተ ልማቶችን በማሟላት፣ በገቢ ማስገኛ ዘርፎች በማሰማራት የተረጋጋና ዘላቂ ህይወት እንዲኖሩ ለማስቻል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የአማራ ልማት ማህበር (አልማ) ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መዝገቡ አንዱዓለም በበኩላቸው፤ ማህበሩ  የህዝብ ችግር ለመፍታት መንግስት የሚያደርገውን ጥረት በመደገፍ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ስራዎችን ከማከናወን ባለፈ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር እየረዳ መሆኑን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም