በቀሪ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች የተጨዋቾች የአካል ብቃት ላይ ትኩረት ይደረጋል - አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ - ኢዜአ አማርኛ
በቀሪ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች የተጨዋቾች የአካል ብቃት ላይ ትኩረት ይደረጋል - አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ
አዲስ አበባ፤መስከረም 8/2017(ኢዜአ)፦ለ35ኛው ቀሪ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች የተጨዋቾች የአካል ብቃት ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ገለጸ።
አሰልጣኙ ይህን የገለፀው ብሔራዊ ቡድኑ ታንዛንያ ላይ ያደረጋቸውን ጨዋታዎች አስመልክቶ ዛሬ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።
"በኢትዮጵያ ያለውን የአጥቂ ችግር ለመፍታት የረዥም ጊዜ ሥራ ይጠይቃል" ያለው አሰልጣኙ፤ ቡድኑ ጨራሽ አጥቂ እንደሌለው ገልጿል።
በኢትዮጵያ የጨራሽ አጥቂ ችግር ለመኖሩ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ግብ አግቢ ሆነው የሚጨርሱት የውጪ አገር ተጨዋቾች መሆናቸው፤ ማሳያ ነው ብሏል።
በዚህም ምክንያት ከታንዛንያና ከዲሞክራቲክ ኮንጎ ጋር ያደረጋቸውን ጨዋታዎች ብዙ የጎል ዕድሎችን ያባከነበት እንደነበር ተናግሯል።
የተጨዋቾች ጉዳትና የአቋም መቀያየር በውጤቱ ላይ የራሱ ተፅዕኖ እንደነበረውም ገልጿል።
ስለሆነም በቀሪ ማጣሪያ ጨዋታዎች ብሔራዊ ቡድኑ የተጨዋቾችን የአካል ብቃት የማስተካከል ሥራና የቡድን ቅንጅት ሥራ ላይ የበለጠ እንደሚሰራ ተናግሯል።
በሞሮኮ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሦስተኛ የምድብ ጨዋታውን ከጊኒ ብሔራዊ ቡድን ጋር መስከረም 27 እና ጥቅምት 5 ቀን 2017 ዓ.ም ያከናውናል።
በሞሮኮ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ 48 አገራት በ12 ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን በማድረግ ላይ ይገኛሉ።