በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነው "ኢሬቻ ኤክስፖ 2017" ከመስከረም 18-24 ቀን በአዲስ አበባ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 8/2017(ኢዜአ)፦ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን "ኢሬቻ ኤክስፖ 2017" ከመስከረም 18 እስከ 24 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ በኤግዚቢሽን ማዕከል እንደሚካሄድ ተገለጸ።   

ኤክስፖውን የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከአገሬ ኢቬንትና ፕሮሞሽን ጋር በመተባበር ነው ያዘጋጀው።

ኤክስፖው የኢሬቻ በዓልና የኢኮኖሚ ትሩፋት እንዲሁም ብዝኃ ባህልን ላይ ያለውን ትስስር በሚያጎላ መልኩ ተዘጋጅቷል ተብሏል።

በኤክስፖው የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ነጋዴዎችና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ታዳሚ እንደሚሆኑ ተገልጿል።

የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ደራራ ከተማ እንደገለጹት፤ የኢሬቻ በዓል ላይ የብዝኃ ባህል የሚንጸባረቅበት ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት በዓል ነው።

በኢሬቻ ኤግዚቢሽንና ባዛር 2017 ላይ ኢሬቻ ከበዓል በተጨማሪ በኢኮኖሚ ላይ ያለው አስተዋጽኦ የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢሬቻና የኢኮኖሚያዊ ትሩፋቶች እንዲሁም የብዝኃ ባህል የሚያሳዩ የተለያዩ ሕዝቦች ባህል የሚንጸባረቅበት መሆኑንም ጠቁመዋል።

የአገሬ ኢቬንትና ፕሮሞሽን ሥራ አስኪያጅ ሐዋኒ እሸቱ በበኩላቸው በኤክስፖው የንግድ፣ የባህል አልባሳትና ጌጣጌጥ፣ የእጅ ሥራዎች፣ የባህላዊ ምግቦች አውደ ርዕዮች ይቀርባሉ ብለዋል።


 

ጎን ለጎንም የሙዚቃ ኮንሰርት፣ የፓናል ውይይትና ሌሎችም ዝግጅቶች እንደሚካሄዱ ገልጸው ከ255 በላይ ድርጅቶች ምርትና አገልግሎታቸውን እንደሚያቀርቡበትም ነው ያስረዱት።

የኢሬቻ በዓል አንዱ የገዳ ሥርዓት መገለጫ ሆኖ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበ ሲሆን በዓሉ የምስጋና፣ የሰላም፣ ፍቅርና አንድነት መገለጫ ነው።

የኢሬቻ በዓል ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት ሲሆን በጸደይ ወቅት በውኃማ አካላትና በበልግ ደግሞ በተራራማ አካባቢዎች የሚከበር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም