ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ አዲስ መልክ ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ተዋንያን ያመጣው ትሩፋት

ኢትዮጵያ የቱሪስት ቀልብ የሚስቡ በታሪክ በባህልና በተፈጥሮ የተትረፈረፈ ጸጋ የተቸራት ሀገር ናት።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ዕምቅ ፀጋዎችን በማልማት፣ በማስተዋወቅ ሀገሪቱ በቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሚነቷን ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።

ኢዜአ የአዲስ አበባ አዲስ መልክ ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ያመጣውን ትሩፋት በተመለከተ የዘርፉ ተዋንያንን አነጋግሯል።

የኢትዮጵያ ሆቴልና መሰል አገልግሎቶች አሰሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ፍትሕ ወልደሰንበት(ዶ/ር) የአዲስ አበባ የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ከሀገሪቱ ዕምቅ ጸጋዎች ጋር ተዳምሮ ለቱሪዝም ዘርፉ ያልተነካ ዕድል ነው ይላሉ።

አሁን ላይ በአዲስ አበባ እየተሰራ ያለው የኮሪደር ልማትና የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ መሰረተ ልማት ይህን ዕድል ለመጠቀም መልካም አጋጣሚዎች እንደሆኑም ገልጸዋል።

በጊዜ የምታንቀላፋዋ አዲስ አበባ አሁን ላይ ሰዎች በማንኛውም ሰዓት ተንቀሳቅሰው መዝናናት መቻላቸውን ዶክተር ፍትሕ ጠቁመው፣ የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ለሀገር ውስጥ ቱሪዝም እምርታ አምጥቷል ብለዋል።

የኮሪደር ልማት መንገዶች ከየትኛውም ሀገር ከተሞች በተሻለ ሳቢና ማራኪ እንደሆኑም በማነጻጸር ይጠቅሳሉ።


 

ባለአራት ኮኮብ የሆነው የመልካ ሆቴል የኦፕሬሸን ማናጀር ነብዩ በለጠ በበኩላቸው የአዲስ አበባ አዲስ መልክ ለውጭ እንግዶቻቸው የደስታና ለሆቴሎችም የኩራት ምንጭ እንደሆነ ያነሳሉ።

በውጭ ሀገር አይተው የሚናፍቁትን የከተማ ልማቶች በአዲስ አበባ በመታየቱ ህዝቡን ያነቃቃ ወደ ሌሎች ሀገራት ለመጓዝ አዲስ አበባን መዳረሻ ላደረጉ መንገደኞችም በከተማዋ ቆይታ እንዲያደርጉ እያደረገ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ ተፈጥሮ ከቸራት አየር በተጨማሪ በአዲስ አበባና በክልሎች የሚሰሩ የቱሪዝም መሰረተ ልማቶች ዘርፉን በዘላቂነት ወደ እምርታ የሚወስድ እንደሆነ ተናግረዋል።


 

ከ10 ዓመታት በላይ በአስጎብኚነት ሙያ የቆየውና የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማህበር ቦርድ አባል ዮናስ ትኩ፣ ከዚህ በፊት ቱሪስቶች አዲስ አበባ ውስጥ ከአንድ ቀን በላይ የሚቆዩበት ዕድል አልነበረም ይላሉ።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ከእንጦጦ፣ አንድነትና ወዳጅነት ፓርኮች፣ የአድዋ መታሰቢያና ሳይንስ ሙዚየም የመሳሰሉ አዳዲስ ገጽታዎች የቱሪስቶች ቆይታ እንዲራዘም ምክንያት ሆነዋል ብለዋል።

ከአዲስ አበባ ውጭ እየተገነቡ ያሉ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶችም ለቱሪዝም ዘርፍ እምርታ ያላቸውን አበርክቶ ጠቅሰዋል።

በተለይም ለስብሰባ የሚመጡ እንግዶች ቆይታ መራዘም በዘርፉ ለተሰማሩ ተዋንያን ትልቅ ትሩፋት ማምጣቱን ገልጸው፣ ማህበሩ አስጎብኚ ሙያተኞችን ለማፍራትም እየሰራ መሆኑ ጠቁመዋል።


 

የቴማ ኢትዮጵያ ቱር አስጎብኚ ድርጀቶች ማኅበር ስራ አስኪያጅ ቴዎድሮስ ሰሎሞን ከ18 ዓመት በላይ ባስቆጠረው የቱሪስት የካበተ ልምዱ አስጎብኚ ሆኖ ማገልገሉን ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት በሆቴልና መሰል አገልግሎት የነበሩ በመሰረተ ልማት ጥራት ማነስና ደረጃቸውን አለመጠበቅ ለአስጎብኚዎች መሳቀቅ፣ ለሀገርም ገጽታ መጉደፍ መንስኤ እንደነበሩ ያስታውሳል።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በከተሞች ልማት ብቻ ሳይሆን በመዳረሻ ልማቶች ላይ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች በዘርፉ ለተሰማሩ ተዋንያን ትልቅ ዕድልና ትሩፋት ይዞ መምጣቱን ገልጸዋል።

የታላቅ ኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ማኅበር ቦርድ አባል ናሆም አድማሱ ቀደም ሲል ከብሔራዊ ቤተ-መዘክርና ከጥቂት ታሪካዊ ስፍራዎች በስተቀር ሌላ መዳረሻ አዲስ አበባ ውስጥ አልነበረም ብለዋል።


 

አሁን ግን በርካታ የቱሪስት መዳረሻ መስህቦች መጨመራቸው የቱሪስቶች ቆይታ እንዲራዘም እያደረገ መሆኑን ገልፀው፣ የኮሪደር ልማቱ በራሱ ለቱሪስቶች ምቾትና እርካታ እየፈጠረ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

አስጎብኚዎችም የደንበኞቻቸውን ደስታ የሚጨምር እና የቆይታ ጊዜ እንዲራዘም መልካም ዕድል መፍጠሩን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም