በክልሉ ለህዳሴ ግድቡ እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ለህዳሴ ግድቡ እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየተደረገ ነው
አዳማ ፤ መስከረም 8/2017 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የማነቃቃት ተግባር እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ገለፀ።
በ2016 በጀት ዓመት የክልሉ ነዋሪ ለግድቡ ግንባታ በቦንድ ግዢ፣ በጥሬ ገንዘብና በዓይነት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ጽሕፈት ቤቱ አስታውሷል።
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ወይዘሮ ቆንጅት በቀለ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት የግድቡ ግንባታ እየተገባደደ በመሆኑ የክልሉ ነዋሪ ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ ድጋፍ ለማድረግ ተነሳስቷል።
በዚህም ግድቡን ከደለል ለመከላከል በተፋሰስ ልማት እና በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እየተሳተፈ መሆኑን አንስተው በቦንድ ግዢ፣ በጥሬ ገንዘብና በዓይነት የሚያደርገውን ድጋፍ እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።
በዚህም በ2016 በጀት ዓመት የክልሉ ህዝብ በቦንድ ግዢ፣ በጥሬ ገንዘብና በዓይነት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
በጽሕፈት ቤቱ የሀብት ማሰባሰቢያ ዳይሬክተር አቶ ዘበርጋ ሂርጳ በበኩላቸው ዘንድሮ ከመደበኛ የግድቡ ግንባታ ሀብት ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ጎን ለጎን ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጀምሮ እስከ ኮሌጆች ድረስ ያሉ ተማሪዎችን ያሳተፈ የንቅናቄ ስራ ለማከናወን በዝግጅት መደረጉን ጠቅሰዋል።
በተለይ የህዳሴ ግድብ የዜጎች አንድነትና ህብረት የታየበት የትብብር ምልክት መሆኑን አዲሱ ትውልድ እንዲገነዘብና በመጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ በሚገኘው ግድብ የራሱን አሻራ እንዲያኖር ያለመ ንቅናቄ ነው ብለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም ለግድብ ግንባታ በቦንድ ግዢ፣ በስጦታና በዓይነት ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት ለማሰባሰብ ታቅዶ የክልሉን ነዋሪ የማስተባበርና የማነቃቃት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግርዋል።
በተጨማሪም ትውልዱ ግድቡ በደለል እንዳይሞላ በተፋሰስ ልማት፣ በአካባቢ ጥበቃና በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በዘላቂነት እንዲሳተፍና የባለቤትነት መንፈስ እንዲያዳብር ለማስቻል እንደሆነም ገልጸዋል።