ቀጥታ፡

ከግብርና ናሙና ቆጠራና ጥናት የሚገኘው መረጃ የዘርፉን ልማትና እድገት ለማፋጠን ፋይዳው የጎላ መሆኑ ተገለጸ

ሚዛን አማን፤ መስከረም 8/2017 (ኢዜአ)፦በቅርቡ በሚጀመረው የግብርና ናሙና ቆጠራና ጥናት የሚገኘው መረጃ የዘርፉን ልማትና እድገት ለማፋጠን ፋይዳው የጎላ መሆኑ ተገለጸ።

ጥናቱ ግብርናው ያለበትን ደረጃ በመለየት ፖሊሲ ለመቅረጽ እና የዘርፉን ችግሮች ለመፍታት የሚረዱ መረጃዎች የሚገኙበት መሆኑም ተመላክቷል።

በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የስልጠና ማዕከል የግብርና ናሙና ቆጠራ ላይ ለሚሳተፉ ባለሙያዎች ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቋል። 

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ባለሙያና የስልጠናው አስተባባሪ ወይዘሮ ሰርካለም አማኑኤል በዚህ ወቅት ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ከመስከረም 10 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የግብርና ናሙና ቆጠራና ጥናት ሥራ ይጀመራል።

የኢትዮጵያ ግብርና ናሙና ቆጠራ ከተካሄደ 22 ዓመታት ማስቆጠሩን አስታውሰው፣ አሁን ላይ ሀገራችን ካለችበት የኢኮኖሚ እድገት አንጻር አዲስ ጥናት ማስፈለጉን ጠቅሰዋል።

ጥናቱ እንደአገር ግብርናው ያለበት ደረጃን በመለየት በዘርፉ የተለያዩ ፖሊሲዎችን ለመቅረጽና ችግሮችን ለመፍታት የሚረዱ መረጃዎች የሚገኙበት መሆኑንም ጠቁመዋል።

እንደ አስተባባሪዋ ገለጻ ለአንድ ዓመት በሚካሄደው የግብርና ናሙና ቆጠራ ሥራ ለሚሳተፉ ባለሙያዎች በተለያዩ የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ስልጠና ሲሰጥ ቆይተዋል።

በቀጣይም ባለሙያዎቹ ለቆጠራ ስራው ወደተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች አንደሚሰማሩ ጠቁመው፣ በግብርና ናሙና ቆጠራና ጥናት የሚገኘው መረጃ የዘርፉን ልማትና እድገት ለማፋጠን ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል። 


 

የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ግርማ ጥላሁን (ዶ/ር) የጥናቱ ሀገራዊ ፋይዳ ከግብርና ልማትና ዕድገት እንቅስቃሴ አንጻር ከፍተኛ መሆኑን ነው የገለጹት።

እንደ ሀገር በእንስሳትና በሰብል ልማት የምርታማነት ደረጃ ተሰንዶ መቀመጡ በዩኒቨርሲቲዎች እና በምርምር ተቋማት ውጤታማ ጥናት ለማድረግ አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል።

ከወቅቱ ጋር የሚሄድ የዳበረ የመረጃ ሥርዓትን መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፣ የግብርና ናሙና ቆጠራ ባለሙያዎች በአግባቡ እንዲሰለጥኑ ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመዋል። 

በኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የሚዛን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ባለሙያና አሰልጣኝ አቶ ኑርልኝ ደመላሽ እንዳሉት፣ በማዕከሉ ስር 600 የሚጠጉ ባሉሙያዎች በአራት ዞኖች ተንቀሳቅሰው መረጃ ይሰበስባሉ።

ለባለሙያዎቹ በሚዛን ቴፒ እና በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በቂ ስልጠና መሰጠቱን ገልጸው፣ ጥናቱ ለግብርና ልማት ሥራ መነሻ የሚሆን መረጃ የሚገኝበት ነው ብለዋል።

በቆጠራው ከሚሳተፉ ሰልጣኞች መካከል እሥራኤል ስምኦን ላለፉት 25 ቀናት የቆጠራ ሥራው ለማከናወን የሚያስችል በቂ እውቀት ማግኘቱን ተናግሯል።

በቀጣይም የትኛውንም መልክዓ ምድር እና የአየር ፀባይ ሁኔታ ተጋፍጦ ትክክለኛ መረጃ ለመሰብሰብ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጧል።

በስልጠናው በአርሶ አደሩ ማሳ ያለውን የሰብል እንዲሁም የእንስሳት ሀብት መረጃ ለመሰብሰብ የሚያስችል ቴክኒክና እውቀት በተግባር ጭምር እንደቀሰሙ የገለጸችው ሌላዋ ተሳታፊ ቅድስት ፍሬው ናት።

የቆጠራውና የጥናት ውጤቱ በግብርናው ዘርፍ የሚኖረው ሀገራዊ ፋይዳ የጎላ በመሆኑ ኃላፊነቷን በአግባቡ ለመወጣት መዘጋጀቷን ተናግራለች።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም