ስኬታማ የክትመት መሰረተ ልማት፤ ለጤናማ የነዋሪዎች ሕይወት

(በቁምልኝ አያሌው)

ከተማ ቋሚና ሠፊ ህዝብ ሰፍሮ የሚኖርበት ቦታ ሲሆን፤ በወጣ ሕግ የሚመራና ራሱን የቻለ አስተዳደር ያለው ወሳኝ የሆኑ የከተማ ልማትና ከተሜነት ጽንሰ ሃሳቦችን ይዟል።

ከተሜነት ከገጠር ወደ ከተማ በሚደረግ የሕዝብ ፍልሰት የሚከሰት የነዋሪነት ቁጥር መጨመር ውጤት መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል። 

በከተሞች የሚኖሩ ዜጎች የቁጥር ዕድገት መኖርም ነዋሪዎች እራሳቸውን  ከሚኖር ሁለንተናዊ ለውጥ ጋር አስማምተው የሚኖሩበት እሳቤ እንደሆነ ይነሳል።

በሌላ በኩልም ከተሜነት የኪነ-ሕንፃ ጠበብቶች እና የከተማ ልማት አሰላሳዮች አሻራ ያረፈበት በሂደት የሚከናወን የመለስተኛና ትላልቅ ከተሞች የዘመናት የዕቅድና ተግባር ሥሪት ድምር ዉጤት መሆኑ ይገለፃል።

የከተማ ልማት ደግሞ ከተማና ከተሜነትን ለነዋሪዎች የአኗኗር ዘይቤ ምቹ ማድረግ የሚያስችል የመሠረት ልማት ግንባታ ማሳለጫ ስልት መሆኑ ይታወቃል።

በድምር ልኬቱም ከተሜነት ሲባል ለዜጎች ዘመናዊ አኗኗር መደላድል የሚፈጥር የድርጊትና የአስተሳሰብ ብልጽግና ሽግግር የሚለካበት የሰው ልጅ የድርጊት አሻራ እንደሆነም ይነሳል።

የከተሞች ውስጠ መልክም ብዝኅ ባህል፣ እምነት፣ ማንነትና የስልጣኔ ስልትን ያቀፉ የሀገረ መንግስት ግንባታና የዕድገት መሸጋገሪያ ድልድይ ናቸው።

ከዚህ ባለፈም ከተሞች የንግድና የአስተዳደር አውድማ ሆነው ሀገርን እና ህዝብን ያገለግላሉ። 

የስነ-ከተማ አጥኚዎች እንደሚሉትም ከተሞች ወንዝ ተከትለው በሰፊ የህዝብ ጥግግት የሚወጠኑ፤ በተማከለ አስተዳደር፣ በአብያተ መንግሥታት፣ አብያተ መቅደሶች እና ቤተ-መቅደሶቻቸው የሚታወቁ ማዕከላት ናቸው።

የከተማ ፕላን ባለሙያው አማን አሰፋ (ዶ/ር) ከተሞች በየዘመናቱ የንግድ፣ የኪነ-ጥበብ እና የኃይማኖት ማዕከላት እንዲሁም የሥልጣኔ መሰረት መሆናቸውን በአንድ ወቅት ለኢዜአ ገልጸዋል።

ለአብነትም ይላሉ ባለሙያው፤ "በኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን ኃይል የመነጨው፣ ፋብሪካና የባቡር ሀዲድ የተዘረጋው በከተሞች ነው። ከተሞች በፈጠራ ጥበባቸው የሕዝብ ስበት ማዕከል ሆነዋል። 

ከድሕረ 20ኛው ክፍለ ዘመን እስከ ዛሬው የዲጂታላይዜሽን አብዮት ዘመንም ከተሞች የአዳዲስ ግኝት፣ የቴክኖሎጂና የዲጂታላይዜሽን አስኳል ሆነው ቀጥለዋል። 

በዚህም የኢንቨስመንት፣ የፋይናንስ፣ የባሕልና የዕውቀት ሜዳ ናቸው። ዘመኑን የዋጁ ኪነ-ሕንጻዎች፣ መንገዶችና የትንሿ ዓለም መልክ መገለጫዎችም ናቸው። ከጥንት እስከዛሬ ከተሞችን የዘመን መመልከቻ መስታውቶች እና አሻራ ማንበሪያ ሰሌዳዎች ሊባሉ ይችላል" ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የከተሜነት ትንበያ እንደሚያመለክተውም እ.አ.አ. በ2050 ከዓለም 70 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ በከተሞች አካባቢው ይኖራል።

ይህም የካርቦን ልቀትና የኃይል ፍጆታ ፍላጎትን በማሳደግ የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን እንደሚያሳደግ አስገንዝቧል።

በዚህም አሁን ባለንበት የ21ኛው ክፍለ ዘመን ዘላቂና ኃይል ቆጣቢ፣ የካርበን ልቀትን የሚቀንሱና ፈጠራ የታከለባቸው በቴክኖሎጂ የዘመኑ የስማርት ሲቲ ግንባታ ስራ ትኩረትን እየሳቡ መጥተዋል።

የ2020 የስማርት ከተማ ግንባታ መረጃ እንደሚያሳየውም ሲንጋፖር፣ ሔልሲንኪ፣ ዙሪክ፣ ኦስሎ፣  አምስተርዳም፣ ኒው ዮርክ እና ሴዑል ከተሞች በቅደም ተከተል የዓለም ምርጥ ሰባት የስማርት ከተማነት ስያሜን ተችረዋል።

በዚህ መነሻነት፤ ይብዛም ይነስ ሀገራት በብርሃን ፍጥነት እያደገ የመጣውን የዜጎች የከተሜነት ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ የስማርት ሲቲ ግንባታን ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ።

ለአህጉራችን አፍሪካ ግን ዜጎች የተሻለ ኑሮን በመሻት ከገጠር ወደከተማ የሚደረግ ፍልሰት ከኋላ ቀር የከተማ መሰረተ ልማት ግንባታ ጋር ተደማሮ ከእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ ሆኖባታል።

የግሎባል ፋየር ፓወር የ2024 ሪፖርትም፤ የግብጿ ካይሮ፣ የኮንጎዋ ኪኒሻሳ፣ የአንጎላዋ ሉዋንዳ፣ የሱዳኗ ካርቱም፣ የኢትዮጵያዋ አዲስ አበባ፣ የኬኒያዋ ናይሮቢ፣ የካሜሮኗ ያውንዲ እና የዑጋንዳዋ ካምፓላ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ የሚኖርባቸው ርዕሰ መዲኖች መሆናቸውን አመላክቷል። 

የዓለም መፃዒ እጣ ፋንታ ይወሰናል የሚል እምነት የተጣለበት የአፍሪካ ፈጣን የህዝብ ቁጥር ዕድገትም ለስራ ብቁ የሆነ የሰው ሃይል የማምጣቱን ያህል ግን በከተሞች ላይ ጫናው እያየለ መምጣቱ ተደጋግሞ ይነሳል።

ለዚህም የቀደምት ሥልጣኔና ከተሜነት አካል የሆነችው አፍሪካ በፈጥነት እያደረገ የመጣውን የህዘብ ቁጥር ታሳቢ ያደረገ የስማርት ሲቲ እና የከተማ መሰረተ ልማት ግንባታን ማሳለጥ የሚያጠያይቅ ጉዳይ አይደለም።

በአህጉሪቷም ‘የምንፈልጋትን አፍሪካ‘ በሚል መርህ እ.አ.አ ከ2013 እስከ 2063 የሚዘልቅ አጀንዳ 2063 የሚመራበት የሀምሳ ዓመታት የልማት ዕቅድ እየተሰራበት ይገኛል።

በሁሉን አቀፍ ዕድገትና ዘላቂ ልማት የበለጸገች አፍሪካን መፍጠር፣ በፓን አፍሪካኒም እሳቤና በአፍሪካ ሕዳሴ ራዕይ አማካኝነት የተሳሰረና ፖለቲካዊ አንድነት ያለው አህጉር እውን ማድረግ እና የአፍሪካን መልካም አስተዳደር የሰፈነበት፣ የሰብአዊ መብቶችና የሕግ የበላይነት የሚከበርበት፣ ፍትሕ የነገሰበትና ዴሞክራሲያዊ አህጉር ማድረግ።

እንዲሁም ሰላሙንና አንድነቱ የጠበቀ አፍሪካን መፍጠር፣ ጠንካራ የባህል ማንነት፣ የጋራ ቅርስና እሴቶች ያሉት ጠንካራ ማህበረሳባዊ የሞራል መሰረት የፈጠረ አፍሪካን ማየት፣ የአፍሪካ ልማት ዜጎችን ማዕከል ያደረገ፣ ሕዝብን በተለይም የወጣቶችና ሴቶችን አቅም የሚጠቀምና ለሕጻናት ክብካቤ ትኩረትን የሰጠ እንዲሆን ማድረግ እና ጠንካራ፣ አንድነቱን የጠበቀ፣ የማይበገርና በዓለም መድረክ ተጽዕኖ ፈጣሪና አጋር የሆነ አፍሪካን መፍጠርም ሰባቱ የአህጉሪቷ አጀንዳ 2063 ዓላማ እና ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው።

በሁሉን አቀፍ ዕድገትና ዘላቂ ልማት የበለጸገች አፍሪካን መፍጠርም ከሰባቱ የአህጉሪቷ 2063 አጀንዳዎች ዓላማ እና የትኩረት መስክ ውስጥ በተሟላ የመሰረተ ልማት ግንባታ ለዜጎች ምቹ የሆኑ ከተሞችን የመፍጠር አካል ነው።

በቅርቡም "ዘላቂ የክትመት ምጣኔ ለአፍሪካ ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ 2063" በሚል መሪ ሀሳብ ከነሐሴ 29 እስከ ጳጉሜን 1 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ የመጀመሪያውን የአፍሪካ ከተሞች ፎረም ተካሂዷል።

የሀገራት መሪዎች፣ ምሁራን፣ የተቋማት እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በዚህ ፎረም ላይ ለአህጉሪቷ ከተሞች ዕድገት ሳንካ የሆኑ ቁልፍና ወሳኝ ችግሮችን መፍትሔ መስጠት የሚያስችሉ ምክረ ሃሳቦች ቀርበው ምክክር ተደርጎባቸዋል። 

በዚህም አህጉራዊ ወንድማማችነትን በማጠናከር ለዜጎች ኑሮ ምቹ የሆኑ ዘመናዊ ከተሞችን በመገንባት የአፍሪካን ከተሞች የዕድገት አቅጣጫና ትስስር የሚያጠናክር ሆኖ ተጠናቋል።

ኢትዮጵያም ባስተናገደችው ፎረም ላይ ከአክሱም፣ ሐረር፣ ጎንደር፣ አዲስ አበባ እና መሰል ጥንታዊ ከተሞቿ የሚመነጨውን የከተሜነት ጽንሰ ሃሳብና እስከ አሁናዊ የኮሪደር ልማት የክትመት ዕድገትና የገጽታ ስራዎችን በተሞክሮነት አጋርታለች።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በአፍሪካ ከተሞች ፎረም መክፈቻ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ የአፍሪካን ዘላቂ የክትመት ሽግግር ለማሳካት በቁርጠኝነት እየሰራች እንደምትገኝ አረጋግጠዋል።

በፎረሙ መልዕክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ የአህጉሪቷ ከተማ ከንቲቦች የነዋሪዎችን ሁለንተናዊ ለውጥ ማረጋገጥ የሚችል ፈጠራ የታከለበት መሰረተ ልማት ማሳለጥ ያስፈልጋል ብለዋል። 

የአፍሪካ ከተሞችን ዕድገት ለማሳለጥ የእርስ በርስ ትብብርና የልምድ ልውውጥ ማህልን ማዳበር ይገባል ያሉት ደግሞ የዩኤን ሃቢታት ዋና ዳይሬክተር አና ክለውዲያ ሮስባች ናቸው።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በፎረሙ በተሰናዳው የከተማ ልማት ፋይናንስ አማራጭ የፓናል ውይይት ላይ ኢትዮጵያ ዘመናዊ ክትመትን ዕውን ለማድረግ የተከተለችው የግሉን ዘርፍ ያሳተፈ የፋይናንስ አማራጭ ስኬት እየተመዘገበበት መሆኑን አብራርተዋል።

መዲናዋን ቀድመው የሚያውቋት አንጋፋው ዲፕሎማት የቀድሞ የሴራሊዮን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ዴቪድ ፍራንሲስ፣ በቻይና ሳውዝኢስት ዩኒቨርሲቲ የኪነ-ሕንፃ ፕሮፌሰር ዋንግ ዢንግፒንግ እና በፈረንሳይ ዓለም አቀፍ ትብብር ተቋም የሰሃራ በታች የክትመት ጉዳዮች ተመራማሪ ሲና ሽልመር(ዶ/ር) ኢትዮጵያ አዲስ አበባን ለማደስ ያከናወነችው የኮርደር ልማት ስራ "አዲስ አበባ አዲስ ሆናብናለች" ብለዋል።

የአፍሪካ ከተሞች የነዋሪዎችን ፍላጎት፣ የከተማነት መስፈርትና ገጽታን ከግምት ውስጥ አስገብተው የተመሰረቱ አይደሉም። 

የከተሞቹ ምስረታም የሰው ልጆችን ሁለንተናዊ ደኅንነት፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ፍላጎት ካለመረዳት በሚመነጭ የከተማ ፕላን ስሪት ጋር የተያያዘ መሆኑም ይነሳል።

በዚህም ከተሞች የፖለቲካል ኢኮኖሚ ማዕከል እንዲሁም የዜጎች የስራ ዕድልና ቴክኖሎጂ ፈጠራ መናኸሪያ መሆናቸውን ታሳቢ ያደረገ ውበት፣ ጽዳትና ለኑሮ ምቹ መዋቅራዊ ዲዛይን ማላበስ ያስፈልጋል።

በአፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ በቂ የከተማ ልማት ማዕቀፍ እና ሕግጋት አለመኖር ለዘመናዊ የከተማ ልማት ዲዛይን ግንባታ ማነቆዎች መካከል ዋነኛው እንደሆነ ይነሳል።

በተለይም ይህ ጉድለት ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፣ የተጠጋጋ የማኅበረሰብ አኗኗርን የያዙ ትልልቅ የአህጉሪቷ ከተሞችን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ-ምህዳራዊ ማዕከልነት የተዛባ እንዲሆን ያደርጋል።

የኢትዮጵያ ከተሞችም ለነዋሪዎች ሁለንተናዊ ለውጥ ምቹ ምኅዳር መፍጠር የሚያስችሉ ዕድሎችን የተጎናጸፉ ሆነው ሳለ በገደምዳሜው ረጅም የዕድሜ ጥንታዊነት፣ ስምና ዝና ብቻ ታቅፈው ቆይተዋል።

በቅርቡ በመዲናዋ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ስራ ግን ስሟን ሳትመስል ለቆየችው አዲስ አበባ "ለነዋሪዎቿ ምቹነትን፤ ለእንግዶቿ አግራሞት" የፈጠረ የአጭር ጊዜ አስደናቂ የልማት ክስተት ሆኖ ተመዝግቧል።

መንግስት አዲስ አበባን እንደ ስሟ “አዲስ እና አበባ ማድረግ ” በሚል መርህ የከተማዋን ገጽታ ለመቀየር ቅድሚያ ሰጥቶ የተለያዩ ስራዎችን አከናውኗል።

ከእነዚህም መካከል የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ኢኒሼቲቭ የሆኑት የገበታ ለሸገር ፕሮጀክቶች ተጠቃሽ ሲሆኑ፤ አሁን ላይ ደግሞ ከተማዋን ወደ ተሻለ ገጽታ እየቀየረ ያለው የኮሪደር ልማት በመከናወን ላይ ይገኛል።

የኮሪደር ልማቱ በዚህም የመንገድ አውታሮች የማስፋፋት ስራ፣ ዘመናዊ የመብራት ዝርጋታ፣ ለከተማው ተጨማሪ ውበት የሚሰጡ የመንገድ ዳር የአረንጏዴ ልማት ስራዎች፣ ዘመናዊ የፍሳሽ ማስወገጃ ስርዓት፣ ምቹ የእግረኛና የብስክሌት መንገድ፣ ያረጁ ህንጻዎች ጥገና እና ማስዋብ በዋናነት እየተከናወኑ ካሉ ስራዎች ውስጥ ይገኙበታል።

የኮሪደር ልማቱ ከ4 ኪሎ ፒያሳና፣ ከ4 ኪሎ አደባባይ በእንግሊዝ ኤምባሲ መገናኛ፣ ከሜክሲኮ ሳር ቤት በጎተራ ወሎ ሰፈር አደባባይ፣ ከ4 ኪሎ በመስቀል አደባባይ ቦሌ ድልድይ እና ከመገናኛ እስከ አዲስ አፍሪካ ኮንቬንሽን ማዕከል ይሸፍናል።

በመጀመሪያው ምእራፍ የተመረቁ የኮሪደር ልማቱ ስፍራዎችም ከወዲሁ አዲስ አበባን የውበት ካባ አጎናጽፈዋታል።

የኮሪደር ልማቱ በግብንታ ሂደትም አዲስ እይታና አስተሳሰብን ያመጣ ነው። በተጨማሪም የኮሪደር ልማቱ ከዚህ ቀደም ፕሮጀክቶችን በተቀመጠላቸው ጊዜና ጥራት ከማጠናቀቅ አኳያ ሲነሱ ለነበሩ ጥያቄዎችም ምላሽ የሰጠ ሆኗል።

የኮሪደር ልማቱ ይዞት የመጣው ሌላኛው እድል ደግሞ ከተማዋ የተደራጀና ዘመናዊ የአደጋና ወንጀል ምላሽ አሰጣጥ ስርዓት እንዲኖራት ማስቻል ነው።

የኮሪደር ልማቱ በሚያልፍባቸው አካባቢዎች የሚገጠሙ ዘመናዊ የደህንነት ካሜራዎችና ምቹ የተሽከርካሪ መንገዶች ወንጀል የመከላከል አቅምን ከማጎልበት ባሻገር ለድንገተኛ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ መስጠት ያስችላሉ።

ከወዲሁ በመጀመሪያው ምዕራፍ ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት የሆኑ የኮሪደር ልማት ስራዎችም በሌሎች ከተሞች ስናያቸው ሩቅ የሚመስሉ የስማርት ከተማ ሃሳቦችን በተግባር ያሳዩ ሆነዋል።

በአጠቃላይ የኮሪደር ልማት ስራው ብዙ ትምህርት የተወሰደበት፣ ማድረግ እንደሚቻል የታየበት፣ የህብረተሰቡ የልማት ጥማት እና ተባባሪነት የታየበት፣ ኢትዮጵያ በራሷ ልጆች፣ በራሷ ሃብት ሃገር መቀየር የሚያስችል አቅም እንዳላት የታየበት ነው።

በዚሁ መነሻነትም እንደ ጥንታዊቷ ጎንደር፣ ውቢቷ ሀዋሳ እና የቱሪስት ማረፊያዋ ቢሾፍቱ ያሉ የኢትዮጵያ ታላላቅና መካከለኛ ከተሞችም የአዲስ አበባን ውብ ገጽታ የኮሪደር ልማት ተሞክሮ ወስደው እየሰሩበት ይገኛል።

በቀጣይም የከተሞች ጽዳትና ውበት የነዋሪዎችን አካላዊ፣ አዕምሯዊና ሞራላዊ ዕድገት የሚበይኑ የሁሉ አቀፍ ማዕከል መሆናቸውን ታሳቢ በማድረግ ዘመናዊ ዕቅድን ከተግባር ያዋደደ ስራ ማሳለጥ ይጠይቃል።

ኢትዮጵያን የሁለንተናዊ የልማት ብርሃን አድማስ፤ የአፍሪካዊያን የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ በልጆቿ ብርቱ ክንዶች ትጋትና ትብብር ድል ይቀዳጁ መልዕክታችን ይሁን።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም