ኢትዮጵያና ፈረንሳይ የትብብር አድማሳቸውን በማስፋት የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ፈረንሳይ የትብብር አድማሳቸውን በማስፋት የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 8/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያና ፈረንሳይ በተለያዩ መስኮች ያላቸውን የሁለትዮሽ ትብብር ለማጎልበት እንደሚሰሩ አስታወቁ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮ-ፈረንሳይ የወዳጅነት ቡድን ዋና ሰብሳቢ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በፈረንሳይ ፓርላማ የአፍሪካ ቀንድ የወዳጅነት ቡድን ፕሬዝዳንት ሴናተር ሁግ ሳሪ ከተመራው የልዑካን ቡድን ጋር ተወያይተዋል።
ውይይቱ የሁለቱ ሀገራት የወዳጅነት ቡድን አባላት በፓርላማ ዲፕሎማሲ፣ በሕዝብ-ለሕዝብ ዲፕሎማሲና የምርጫ ስርዓትና አፈጻጸምን ጨምሮ በሌሎች ዘርፎች ያላቸውን ትብብር ማጠናከር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው።
አምባሳደር ዲና ለረጅም ዓመታት የዘለቀው የኢትዮጵያና የፈረንሳይ ወዳጅነት የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች ብሔራዊ ጥቅምን መሠረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድና በተቀረው ዓለም የዜጎችን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ አሸባሪዎችን ለመዋጋት ከፈረንሳይና ከሌሎች አጋር ሀገራት ጎን ትቆማለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር መተባበርንና የጋራ ጥቅምን መሰረት ያደረገ ግንኙነት በመፍጠር ዘላቂ አካባቢያዊ ሰላም እንዲረጋገጥ አበክራ እየሰራች መሆኑንም ነው አምባሳደር ዲና የገለጹት።
ኢትዮጵያ የዜጎችን ሁለንተናዊ አቅም የሚያጎለብቱ የተለያዩ የሪፎርም ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደምትገኝና ወዳጅ ሀገራት ለሪፎርሙ ውጤታማነት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በፈረንሳይ ፓርላማ የአፍሪካ ቀንድ የወዳጅነት ቡድን ፕሬዝዳንት ሴናተር ሁግ ሳሪ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ለፈረንሳይ ታሪካዊ አጋር ናት ሲሉ ገልጸዋል።
ፈረንሳይ በአፍሪካ ቀንድና አፍሪካ ከአጋሮቿ ጋር በትብብርና የጋራ ብሔራዊ ጥቅምን መሰረት ባደረገ መልኩ እንደምትሰራ አመልክተዋል።
ፈረንሳይ በአፍሪካ ቀንድና አፍሪካ ሽብርተኞችን ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ትሰራለች ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ለጀመረቻቸው የተለያዩ የሪፎርም ስራዎችን ድጋፍ እንደምታደርግ ሴናተር ሁግ መግለጻቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1897 መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።