ቀጥታ፡

በግብርና ናሙና ቆጠራ የሚሰማሩ ባለሙያዎች በታማኝነት እና በሃላፊነት ስሜት ሀገራዊ ተልዕኳቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 7/2017(ኢዜአ)፦በግብርና ናሙና ቆጠራ የሚሰማሩ ባለሙያዎች በታማኝነት እና በሃላፊነት ስሜት ሀገራዊ ተልዕኳቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ።

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክ አገልግሎት በግብርና ናሙና ቆጠራ የሚያገለግሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ 43 ሺህ 500 ግለሰቦችን መልምሎ በ45 ዩኒቨርሲቲዎች አሰልጥኗል።

በዛሬው እለት ደግሞ ለመጨረሻ ዙር በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ዩኒቨርሲቲ ያሰለጠናችውን 1 ሺህ 354 ሰልጣኞች አስመርቋል።

የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ ተሰማ ኡርጌሳ፤ የዕለቱ ተመራቂዎች ለ25 ቀናት የሰለጠኑ የመጨረሻ ዙር ሰልጣኞች ሲሆኑ በአዲስ አበባና ሸገር ከተማ መረጃ የሚሰበስቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

የግብርና ናሙና ቆጠራው ከ22 አመት ወዲህ በቴክኖሎጂ ታግዞ የሚካሄድ ስራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዘርፉ ለአገር ኢኮኖሚ ያለውን ድርሻ በትክክል ለይቶ ለማወቅ የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም በግብርና ናሙና ቆጠራ የሚሰማሩ ባለሙያዎች በታማኝነት እና በሃላፊነት ስሜት ሀገራዊ ተልዕኳቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ተወካይ ዶክተር ተመስገን ወንድሙ፤ ሰልጣኞች የተጣለባቸውን ኅላፊነት በአግባቡ በመገንዘብ በጥራት እና በላቀ ሃላፊነት እንዲከውኑ ጠይቀዋል።


 

ከሰልጣኖች መካከል ይታየው ሞላ እና ዘይነባ አራጌ፤ ስልጠናው በጽንሰ ሃሳብ እና በተግባር የታገዘ መሆኑን ጠቅሰው የሚሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት፣ በታማኝነትና በከፍተኛ ሃላፊነት ለመከወን መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም