የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ይፋ መደረጉ በዘርፉ ያለውን ዕምቅ አቅም በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል ነው - ኢዜአ አማርኛ
የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ይፋ መደረጉ በዘርፉ ያለውን ዕምቅ አቅም በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 7/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ይፋ መደረጉ በዘርፉ ያለውን ዕምቅ አቅም በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል መሆኑ ተገለጸ።
የቱሪዝም ሚኒስቴር ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ካዘጋጀው ዓውደ ርዕይ በተጓዳኝ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሳተላይት አካውንትን ይፋ አድርጓል።
በዚሁ ሁነት ላይ ተገኝተው ኢዜአ ያነጋገራቸው የዘርፉ ተዋንያን ኢትዮጵያ ተፈጥሮአዊ፤ ባህላዊና ታሪካዊ የመስህብ ሀብቶች ቢኖሯትም እስካሁን በቅጡ አልምታ ያልተጠቀመችበት መሆኑን አንስተዋል።
የቱሪዝም ልማትን አጠቃላይ ዕድልና መረጃዎችን የሚሰንደው የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት አለመኖሩ ደግሞ ዘርፉን ጎድቶት መቆየቱን ጠቅሰው አሁን ይፋ መሆኑ ትልቅ ስኬት መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ሆቴል አሰሪዎች ፌደሬሸን ፕሬዘዳንት ፍትሕ ወልደሰንበት (ዶ/ር)፤ የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ከፍተኛ የስራ ዕድል የሚፈጥሩ ቢሆንም የመረጃ ጉድለት ትልቅ ሳንካ ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በመሆኑም የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ይፋ መደረጉ ለዘርፉ እድገት ተስፋ የሰነቀ መሆኑን ገልጸዋል።
የመልካ ሆቴል ኦፕሬሽን ማናጀር ነብዩ በለጠ፤ በበኩላቸው የሳተላይት አካውንት ይፋ መሆን ለሆቴልና ቱሪዝም ዘርፉ እድገት መነቃቃት ወሳኝ ድርሻ የሚኖረው መሆኑን ተናግረዋል።
የታላቅ ኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ማኅበር ቦርድ አባል ናሆም አድማሱ፤ ኢትዮጵያ የሳተላይት አካውንት ይፋ ማድረጓ በዘርፉ ያላትን ዕምቅ አቅም በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችላት መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በዩኔስኮ በተመዘገቡ ቅርሶቿም ሆነ በሌሎች የቱሪስት መዳረሻዎች ቀዳሚ ሀገር ብትሆንም ዘርፉን በአግባቡ ሰንዳ ባለማስተዋወቋ ዕምቅ አቅሟን ሳትጠቀም መቆየቷን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ የቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማኅበር የቦርድ አባል ዮናስ ትኩ፤ የሳተላይት አካውንቱ በመረጃ ላይ የተመሰረተ እና በዕቅድ የተመራ የቱሪዝም ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም በዘርፉ ለተሰማሩ ተዋኒያን ይበልጥ ኢንቨስትመንታቸውን ለማስፋትና ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጉልህ ፋይፈዳ እንደሚኖረው ነው ያነሱት።