ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ከቱሪዝም ባሻገር ለግብርና እና ኮንስትራክሽን ዘርፎች መነቃቃት የሚያግዝ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 7/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ከቱሪዝም ባሻገር ለግብርና እና  ለኮንስትራክሽን ዘርፎች መነቃቃት የሚያግዝ መሆኑን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ገለጸ፡፡

የዓለም የቱሪዝም ቀንን በማስመልከት ከኢጋድና ከተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጋር በመተባበር የተዘጋጀው ኤግዚቢሽን በዐድዋ ድል መታሰቢያ ተከፍቷል፡፡

በዚሁ ሁነት ላይ የተገኙት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተወካይ ጆኦፍሬይ ማንያራ፤ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሳተላይት አካውንት የቱሪዝም ዘርፉን ለማጠናከር ጉልህ ሚና ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሳተላይት አካውንት የኢትዮጵያን የቱሪዝም አቅም ለማወቅ እንዲሁም ለግብርና እና ኮንስትራክሽን ዘርፎች መነቃቃት አበርክቶውን ዘርዝረዋል።


 

የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በታሪካዊ፣ በተፈጥሯዊና ባህላዊ ሀብቶቿ እንዲሁም በቱሪዝም መዳረሻነት ሰፊ ሃብት ያላት መሆኗን ገልጸዋል።

የቱሪዝም ሃብት የውጭ ምንዛሪ ምንጭ፣ የስራ እድል መፍጠሪያ ዘርፍና የሀገር የእድገት ሙሰሶ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ይህንን እምቅ ሃብት በማልማት ከዘርፉ የሚገባትን ጥቅም ለማግኘት አሁን ላይ በመንግስት እየተደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ በረከት ፍስሀጽዮን፤ መንግስት የኢትዮጵያን ዕምቅ ፀጋዎች ለይቶ በማልማት የምጣኔ ሃብት እድገት ዋነኛ ዘርፍ አድርጎ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሳተላይት አካውንትም በአገልግሎት ዘርፉ የሚገኘውን ገበያ ለማሻሻልና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ወሳኝ ድርሻ የሚኖረው መሆኑን ጠቅሰዋል።


 

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ (ዶ/ር)፤ በበኩላቸው የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት የቱሪዝም ዘርፉን አንድ ደረጃ ወደ ፊት የሚያራምድ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምት፣ የሰው ዘር መገኛ፣ የፓን አፍሪካ ንቅናቄ መሰረትና የህብረብሄራዊነት መገለጫ ሀገር መሆኗን ጠቅሰው የተፈጥሮ ሀብቶቿን፣ ባህልና ወጎቿን በተጀራጀ መንገድ አገልግሎት ላይ ማዋል ሳትችል ቆይታለች ብለዋል።

በመሆኑም የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ቀጣይነት ያለውና የማያቋርጥ የተደራጀ የቱሪዝም ስታስቲክስ መረጃ በመያዝ የተሳለጠ የቱሪዝም መረጃ ፍሰት እንዲኖር የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም