ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ የምታደርግባቸው ቀናት ይፋ ሆኑ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 7/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የሚያደርግባቸው ቀናት ዛሬ ይፋ ተደርገዋል።

24ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከ20 ዓመት በታች የሴካፋ ዞን ማጣሪያ በታንዛንያ ከመስከረም 26 እስከ ጥቅምት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ይካሄዳል።

ኢትዮጵያ በምድብ 2 ከዩጋንዳ፣ ብሩንዲና ደቡብ ሱዳን ጋር ተደልድላለች።

የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ የእግር ኳስ ማህበራት ምክር ቤት(ሴካፋ) የማጣሪያ መርሐ ግብሩን ዛሬ ይፋ አድርጓል።

ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ጨዋታዋን መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም ከዩጋንዳ ጋር ታከናውናለች።

ብሔራዊ ቡድኑ መስከረም 29 ቀን 2017 ዓ.ም ከደቡብ ሱዳን እንዲሁም ጥቅምት 1 ቀን 2017 ዓ.ም ከብሩንዲ ጋር ይጫወታል።

በማጣሪያው በምድብ አንድ ታንዛንያ፣ ሩዋንዳ፣ ሱዳን፣ ጅቡቲና ኬንያ ተደልድለዋል።

የማጣሪያ ጨዋታዎቹ በኪኖንዶኒ ሙኒሲፓል ካውንስልና በሜጀር ጄኔራል ኢሳሙዮ ስታዲየሞች እንደሚካሄዱ ሴካፋ አስታውቋል።

አሰልጣኝ ስዩም ከበደ በማጣሪያ ውድድሩ የሚሳተፈውን የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሆነው መሾማቸውን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ትናንት ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።

ዐቢይ ካሣሁንና አምሳሉ እስመለዓለም ረዳት አሰልጣኝ በመሆን ተሹመዋል።

አሰልጣኝ ስዩም ብሔራዊ ቡድኑ ለማጣሪያ ውድድሩ ለሚያደርገው ዝግጅት ለ38 ተጫዋቾች የመጀመሪያ ዙር ጥሪ አድርገዋል።

ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች ከዛሬ ጀምሮ ዝግጅታቸውን እንደሚጀምሩ ፌዴሬሽኑ አመልክቷል።

በሴካፋ ዞን ማጣሪያ ለፍጻሜ የሚደርሱ ሁለት ሀገራት በአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ያልፋሉ።

በአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ 12 ሀገራት ይሳተፋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም