ቀጥታ፡

የግብርና ናሙና መረጃ አሰባሰብ ሂደቱ በዘርፉ ያለውን አቅም በመለየት ማነቆዎችን ለመፍታት ያግዛል

ሆሳዕና፤ መስከረም 7/2017ዓ (ኢዜአ)፦የግብርና ናሙና መረጃ አሰባሰብ ሂደቱ በዘርፉ ያለውን አቅም በመለየት ማነቆዎችን ለመፍታትና ውጤታማ ተግባራትን ለማከናወን የሚያግዝ መሆኑን የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

አገልግሎቱ ከዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የግብርና ናሙና መረጃ አሰባሰብ ላይ ለመረጃ ሰብሳቢዎችና ተቆጣጣሪዎች ሲሰጥ የነበረውን ስልጠና አጠናቋል፡፡

በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የሆሳዕና ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ካሳሁን አሰፋ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ የግብርና ናሙና ቆጠራ ስራው ሀገሪቱ በዘርፉ ያላትን አቅም መለየትን ዓላማ ያደረገ ነው፡፡

በአገሪቱ ላለፉት 22 ዓመታት የመረጃ ዳሰሳ ጥናት ሳይከናወን መቆየቱን አስታውሰው የግብርና ናሙና መረጃ አሰባሰብ ሂደቱ በዘርፉ ያለውን አቅም በመለየት ማነቆዎችን በመፍታት ውጤታማ ተግባራትን ለማከናወን ያግዛል ብለዋል፡፡

በግብርናው ዘርፍ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶች ተጨባጭ ውጤት እንዲያመጡ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች በቆጠራ ስራው ተለይተው መፍትሄ እንደሚበጅላቸውም ገልጸዋል፡፡

በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ለውጥ ለማስመዝገብ የተጀመረውን ጥረት ከማገዝ አኳያም በጎ ተፅዕኖ እንደሚፈጥር ገልጸው ለመረጃ አሰባሰብ ሂደቱ ስኬታማነት በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳዊት ሀየሶ በበኩላቸው የግብርና መረጃ ዳሰሳ ጥናት የማሰባሰብ ስራ በዘርፉ የታቀዱ  ተግባራትን እውን በማድረግ ሀገሪቱን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር ያለው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡


 

የመረጃ ማሰባሰብ ስራው የሚያስገኘውን ጥቅም በመረዳት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ሰልጣኞች በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው ያገኙትን እውቀት ተጠቅመው ተገቢነት ያለውና ተአማኒነት ያለው መረጃ ማሰባሰብ እንደሚጠበቅባቸውም አስረድተዋል፡፡

በመረጃ ማሰባሰብ ስልጠናው ላይ ከተሳተፉት መካከል ከከምባታ ዞን ሀደሮ ከተማ ወጣት መሰረት በየነ በሰጠችው አስተያየት የመረጃ ማሰባሰብ ስራው ለሀገር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው፡፡

በግብርናው ዘርፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመዘገበ ያለውን ውጤትና ተግዳሮት በተጨባጭ ለመለየት ተዓማኒ የሆነ መረጃ ማሰባሰብ ያስፈልጋል ብላለች፡፡

በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ላለፉት 25 ቀናት በተሰጠው ስልጠና ላይ ከ 1 ሺህ 300 በላይ የመረጃ ሰብሳቢዎችና ተቆጣጣሪዎች   መሳተፋቸውም ተገልጿል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም