ቀጥታ፡

የዜጎችን የጤና አገልግሎት የተሟላና ደኅንነቱ የተጠበቀ የሚያደርጉ አሰራሮች እየተተገበሩ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 7/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የዜጎችን የጤና አገልግሎት የተሟላና ደኅንነቱ የተጠበቀ የሚያደርጉ አሰራሮች እየተተገበሩ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

የጤና ሚኒስቴር "ደኅንነቱ የተረጋገጠ የተሟላ ምርመራ ለተሟላ ጤንነት" በሚል መሪ ሃሳብ ዓለም አቀፉን የህሙማን ደኅንነት ቀን አክብሯል።

በሁነቱ ላይ የተገኙት በጤና ሚኒስቴር የጤና ሥርዓት ኢኖቬሽንና ጥራት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር አባስ ሀሰን፤ ዜጎች ጥራት ያለው ፍትሕዊና ደኅንነቱ የተረጋገጠ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የጤና ሥርዓት በመዘርጋት የዜጎችን ጤና በማሻሻል ደኅንነቱ የተጠበቀ የጤና አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ምኅዳር እየተፈጠረ ይገኛል ብለዋል።

ከምርመራ ጀምሮ ህሙማን ተገቢና ትክክለኛ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የቴክኖሎጂ አሰራሮችን መተግበርን ጨምሮ የሙያተኛ አቅም ግንባታና የሕክምና መገልገያ ግብዓት አቅርቦት የማሟላት ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዶክተር ተግባር ይግዛው፤ የሕክምና ሙያተኞችን አገልግሎት ማሻሻል የሚያስችል ቀጣይነት ያለው ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

በእስካሁኑ ሂደት ከ20 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የጤና ሙያተኞች በተለያየ ዘዴ ስልጠና መሰጠቱን አስታውሰው ቀጣይነት እንደሚኖረው ተናግረዋል።

ዓለም አቀፉ የህሙማን ደኅንነት ቀን በኢትዮጵያ ለ6ኛ ጊዜ በተለያዩ መርሃ ግብሮች በመከበር ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም