ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል የ2017 የትምህርት ዘመን ተጀመረ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 7/2017(ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል የ2017  የትምህርት ዘመን በሁሉም የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች ዛሬ ተጀምሯል።

በሸገር ከተማ አስተዳደር ፉሪ ክፍለ ከተማ በኩራቡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት  የ2017 የትምህርት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሄዷል፡፡

በመርኃ ግብሩ ላይ የኦሮሚያ ክልል  ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ  ዶክተር ቡልቶሳ ሂርኮ፣ የሸገር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ግርማ ሃይሉ፣ የሸገር ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽህፈት ቤት ሃላፊ ፊራኪያ ካሳሁንና ሌሎች የትምህርቱ ማህበረሰብ ተገኝተዋል።

የቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ቡልቶሳ ሂርኮ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ጥራትን በማስጠበቅ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እየተሰራ ነው ብለዋል። 


 

ለዚህም በክልሉ ደረጃቸውን የጠበቁ የመማሪያ ክፍሎችን፣ የማስተማሪያ ቁሳቁሶችን፣የመማሪያ መጽሀፎችንና የተማሪዎች የምገባ ስራ በስፋት ለመስራት ዝግጅት ተጠናቋል ብለዋል።

በተለይም ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት ከፍተኛ ሃብት በመመደብ በሁሉም አካባቢ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ተደራሽ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ባለፉት ሶስት ዓመታት  ከ15 ሺህ በላይ  የቡኡራ ቦሩ ትምህርት ቤት በመገንባት ተደራሽነትን ማስፋት የተቻለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ የተማሪዎች ውጤት መሻሻል እያሳየ መሆን ገልጸው፤ ወደ ሚፈለገው ደረጃ ለማሳደግ  በዘንድሮ የትምህርት ዓመት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ይበልጥ እንዲጠናከር ጠይቀዋል፡፡

በክልሉ በዘንድሮ አመት ከ12 ሚሊየን በላይ ተማሪዎችን ትምህርት የጀመሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ወላጆች ልጆቻቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ትምህርት ቤት ከመላክ ባለፈ የተማሩትን በአግባቡ አጥንተው ውጤታማ እንዲሆኑ ሊያግዟቸው ይገባል ብለዋል፡፡

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም