የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ህልፈተ ሕይወት የተሰማውን ሃዘን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ህልፈተ ሕይወት የተሰማውን ሃዘን ገለጸ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 7/2017(ኢዜአ)፦ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ህልፈተ-ሕይወት የተሰማውን ሐዘን ገልጿል፡፡
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ዕንቁ ምሁራን መካከል በቀዳሚነት ተርታ የሚጠቀሱ ናቸው፤ ተመራማሪ፣ መምህር፣ በሳል ፖለቲከኛና ብቁ አመራር ነበሩ ብሏል ምክር ቤቱ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ።
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ሀገራቸውን በተለያዩ መስኮች በትጋትና በሀገር ፍቅር ስሜት ማገልገላቸውን የገለጸው ምክር ቤቱ ከደርግ መንግስት መወደቅ ማግሥት በተቋቋመው የሽግግር መንግስት የተወካዮች ምክር ምክር ቤት አባል በመሆን በሀገሪቱ ሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር እንዲሳካ ጉልህ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን አስታውሷል።
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የደቡብ ሕብረት እና የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ሕብረት ፓርቲ ሊቀመንበር ሆነው ባገለገሉበት ወቅት በቀድሞ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሃዲያ ዞን የስቄ ቁጥር ሁለት ምርጫ ክልል ሕዝብን በመወከል በ2ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ከ1993 እስከ 1997ዓ.ም) እንደዚሁም በ3ኛው ምክር ቤት (ከ1998 እስከ 2002ዓ.ም) አባል በመሆን የሕዝብ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያው ጥያቄዎችና ፍላጎቶች እንዲመለሱ ከሕዝብ የሰጣቸውን ኃላፊነትና አደራ በትጋትና በቁርጠኝነት ስሜት ተወጥተዋል፡፡
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በሀገሪቱ ፖለቲካ ንቁ ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን በሀገሪቱ ሠላማዊ የፖለቲካ ባህል እንዲዳብር ፤ የመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲ ስርዓት እንዲጠናከር የራሳቸውን አሻራ አስቀምጠው ብሏል ምክር ቤቱ።
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ለሀገርና ለሕዝብ ኖረው ሙሉ ጊዚያቸውን የሰጡ ሀገር ወዳድ ብርቱ ኢትዮጵያዊ ነበሩ ፡፡
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ከዚህ ዓለም ድካም በአካል ቢለዩንም በትምህርት፣ በፖለቲካ አመራርና በሌሎች ዘርፎች ያስመዘገቧቸው ድሎችና አኩሪ ሥራዎቻቸው ዘውትር እንድናስታውሳቸው ታሪክ ግድ ይለናል ሲልም ምክር ቤቱ አጽንኦት ሰጥቷል፡፡
የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ህልፈተ ሕይወት የተሰማውን ጥልቅ ሐዘን እየገለፀ ለቤተሰቦቻቸው፣ ለዘመድ አዝማድ ወዳጆች እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መፅናናትን ተመኝቷል።