ቀጥታ፡

የቻይናው ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ ለኢትዮጵያዊያን የግንባታ ባለሙያዎች ሥልጠና መስጠት ጀመረ  

አዲስ አበባ፤ መስከረም 7/2017(ኢዜአ)፦የቻይናው  ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ (ሲሲሲሲ) ለኢትዮጵያዊያን የግንባታ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠና መስጠት ጀመረ።

ኩባንያው ሥልጠናውን የሚሰጠው ሉባን ወርክሾፕ ከተሰኘው የቻይና ኩባንያ እንዲሁም ከፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢኒስቲትዩት ጋር በመተባር ሲሆን ከ100 በላይ ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።        

በሴጉል የታለንት ልማት ፕሮጀክት አማካኝነት የሚተገበረው ስልጠና ለሚቀጥለው አንድ ወር በግንባታ፣ በሰርቬይንግ፣ ቢውልዲንግ ማቴሪያል ቴስቲንግ እንዲሁም በሜካኒካልና መሳሪያዎች ጥገና ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።   

በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ የኢኮኖሚ እና ንግድ ጉዳዮች ሚኒስትር አማካሪ ያንግ ዪ ሃንግ፤ የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ከልማት ሥራዎች ጎን ለጎን ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የቻይና መንግሥት የሚያበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

  

የቻይናው ኮሙኒኬሽን ኮንትራክሽን ኩባንያ በዛሬው ዕለት ይፋ ያደረገው የሥልጠና መርሃ ግብርም ለዚህ ሁነኛ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል።   

በመሆኑም የስልጠናው ተሳታፊዎች በሚያገኙት እውቀት ትልቅ አቅም በመፍጠር የአገሪቷን እድገት የሚያፋጥኑ የግንባታ ስራዎችን ለማከናወን የሚያስችል ነው ብለዋል።   

በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ዘርፍም ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እየሰራች መሆኑን ጠቅሰው እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ2021  ጀምሮ በሉባን ወርክሾፕ በኩል ከ1 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን መሰልጠናቸውን ጠቅሰዋል።    

በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ማርታ ወልዴ፤ ለኢንዱስትሪዎች አቅሙ የተገነባ የሰው ኃይል ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።   


 

ለዚህም የስርዓተ ትምህርት ክለሳና የሙያና የብቃት ደረጃ አሰራር ክለሳ ተደርጓል ብለዋል።     

የፌደራል የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢኒስቲትዩት የሪሰርችና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ሙሉጌታ፤ ከመሰል ኩባንያዎች ጋር የሚደረጉ ትብብሮች ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች ከአገራቸው አልፎ በሌሎች አገራት የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ትልቅ እድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል። 


 

የስልጠናው ተሳታፊዎችም በተሰጣቸው እድል አመስግነው አጋጣሚውን በአግባቡ እንጠቀምበታለን ሲሉ ተናግረዋል።

 የስልጠናው መሰጠት በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት ከማጠናከር ባለፈ የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የልማት መስኮች ያላቸውን ተሳትፎ የሚያጠናክር መሆኑ ተመላክቷል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም