ቀጥታ፡

​​​​​​​የኢትዮ-እስራኤል ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ትብብር በጤናው ዘርፍም ተጠናክሮ ይቀጥላል -ቶመር ባርላቪ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 7/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮ-እስራኤል ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ትብብር በጤናው ዘርፍም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በኢትዮጵያ እስራኤል ምክትል አምባሳደር ቶመር ባርላቪ ገለጹ።

የእስራኤል የሕክምና ልዑካን ቡድን በአዲስ አበባ አለርት ኮንፕረሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለሕክምና ሙያተኞች የጨቅላ ሕፃናት ህክምና ላይ የልምድ ማጋራት ስልጠና መስጠት ጀምሯል።

በአዲስ አበባ ለአንድ ሳምንት በሚሰጠው ስልጠና ላይ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ሆስፒታሎች የተውጣጡ 30 የጨቅላ ሕፃናት የሕክምና ሙያተኞች በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።

በቀጣይም ከአዲስ አበባ በተጨማሪ ባሕር-ዳር እና ደሴን ጨምሮ በሌሎች ከተሞችም ለጨቅላ ሕፃናት የሕክምና ሙያተኞች ስልጠና እንደሚሰጥ ተነግሯል።

በዚሁ ጊዜ በኢትዮጵያ የእስራኤል ምክትል አምባሳደር ቶመር ባርላቪ፤ ኢትዮጵያ የጨቅላ ሕፃናትን ሞት ለመቀነስ በምታደርገው ጥረት እስራኤል የሕክምና ቁሳቁስና የስልጠና ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል።

የእስራኤል የሕክምና ልዑክ በኢትዮጵያ ቆይታቸው የሚሰጡት የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ እና ስልጠናም ሀገራቱ ያላቸውን ዘርፈ ብዙ የዲፕሎማሲ ትብብር የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።  

የኢትዮ-እስራኤል የዲፕሎማሲ ትብብርም በቴክኖሎጂ፣ በትምህርት፣ በግብርና እና ሌሎች መስኮች ረዥም ዓመታትን የተሻገረ ታሪካዊ ወዳጅነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ተናግረዋል። 

ከዚህ ባሻገርም እስራኤል ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ታሪካዊ ወዳጅነት በቴክኖሎጂ ምኅዳር ግንባታ፣ በስራ ዕድል ፈጠራ እና በጤና አጠባበቅ መስክ አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።


 

በአላርት ኮንፕረሄንሲቪ ስፔሻላዚድ ሆስፒታል የሕክምና አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር ፀጋየ ገብረአናንያ፤ ከእስራኤል የሕክምና ልዑካን ቡድን ጋር የሚሰጠው የንድፈ ሃሳብና የተግባር ስልጠናም የጨቅላ ሕፃናት ሞትን ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ከሰልጣኞች መካከል በአላርት ኮንፕርሄንሲቪ ስፔሻላዚድ ሆስፒታል የህፃናት ስፔሻሊስት ሀኪም ዶክተር ዓለም ግዛቸው፤ ስልጠናው ዕውቀትና ክህሎትን በማዳበር የሕፃናትን ጤና ለማስጠበቅ አቅም ይፈጥራል ብለዋል። 

በእስራኤል የሕክምና ሙያተኞች ልዑካን ቡድንም የሚሰጠው ስልጠናው በቴክኖሎጂ አጠቃቀምና ልምድ ልውውጥ ትብብርን የሚያሳደግ መሆኑን ገልጸዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም