ፕሮፌሰር በየነ ዼጥሮስ በኢትዮጵያ ፖለቲካ በሃሳብ ልእልና ተፎካክሮ ማሸነፍ እንደሚቻል በተግባር ያሳዩ ታላቅ ፖለቲከኛ ነበሩ - ኢዜአ አማርኛ
ፕሮፌሰር በየነ ዼጥሮስ በኢትዮጵያ ፖለቲካ በሃሳብ ልእልና ተፎካክሮ ማሸነፍ እንደሚቻል በተግባር ያሳዩ ታላቅ ፖለቲከኛ ነበሩ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 7/2017(ኢዜአ)፦ ፕሮፌሰር በየነ ዼጥሮስ በኢትዮጵያ ፖለቲካ በሃሳብ ልእልና በሰላማዊ መንገድ ተፎካክሮ ማሸነፍ እንደሚቻል በተግባር ያሳዩ ታላቅ ፖለቲከኛ ነበሩ ሲሉ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ደስታ ዲንቃ ገለጹ።
የአንጋፋውን ፖለቲከኛና መምህር ፕሮፌሰር በየነ ዼጥሮስ ህልፈት ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ጨምሮ በርካታ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ፖለቲከኞችና ታዋቂ ግለሰቦች ሃዘናቸውን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ደስታ ዲንቃ፤ ፕሮፌሰር በየነ ዼጥሮስ በኢትዮጵያ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ትልቅ አሻራ ያሳረፉ ታላቅ ሰው ነበሩ ሲሉ ተናግረዋል።
በኢትዮዽያ ገንቢ የፖለቲካ ባህል ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ የሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ምልክት እንደነበሩም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ከፈተናዎቿና ከውጭ ጫናዎች መላቀቅ የምትችለው የውስጥ አንድነቷን ስታጠናክር ነው ብለው ያምኑ እንደ ነበር አስታውሰው ህልፈታቸው ለሀገርም ሆነ ለፓርቲያቸው ጉድለት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የእርሳቸው ህልፈት ለሀገርም ሆነ ለፓርቲያቸው ትልቅ ጉድለት የፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው ለሁላችንም ከፍተኛ ሃዘን ፈጥሯል ሲሉም ተናግረዋል።
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በማድረግ እንደሚታወቁና አንድነትን የሚያጠናክሩ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል።
የሀገርንና የህዝብ ጥቅም በማስቀደም ከተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ጥምረት በመፍጠር አብሮ የመስራት አቅምና ችሎታ የነበራቸው ታላቅ ፖለቲከኛም ነበሩ ብለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት፣ በመንግስታዊ የስራ ሃላፊነት የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ በመሆን ማገልገላቸውን አንስተው እስከ ህልፈተ ህይወታቸው የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል።
በመሆኑም የጋራ ምክር ቤቱ በፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ህልፈት የተሰማውን ሃዘን በመግለፅ ለመላ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው መጽናናትን ተመኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ በፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ሃዘን በመግለፅ በኢትዮዽያ ገንቢ የፖለቲካ ባህል ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ የሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ምልክት ነበሩ ብለዋል።