በሆስፒታሉ አንድ ሺህ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነፃ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ህክምና መስጠት ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በሆስፒታሉ አንድ ሺህ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነፃ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ህክምና መስጠት ተጀመረ
ወልዲያ፤ መስከረም 7/2017(ኢዜአ)፦ የወልዲያ ጠቅላላ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አንድ ሺህ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነፃ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ህክምና በዘመቻ መስጠት መጀመሩን ሆስፒታሉ አስታወቀ።
የሆስፒታሉ የዓይን ህክምና ባለሙያና የዘመቻው አስተባባሪ አቶ ሰለሞን በላይ እንደገለጹት፤ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ህክምና ዘመቻው ከመስከረም 7 እስከ 11/2017 ዓ.ም የሚቆይ ነው።
በዚሁ ህክምናም በሰሜን ወሎና ወልዲያ ከተማ ለሚገኙ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ህሙማን ህክምና ለመስጠት ስራው መጀመሩን ጠቅሰው፤ በዘመቻ በሚሰጠው የነፃ ህክምናም አንድ ሺህ ሰዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል።
በህክምናውም 52 የዘርፉ ባለሙያዎች እየተሳተፉ መሆኑን አመልክተው፤ ታካሚዎች ቀደም ብለው መለየታቸውንም ገልጸዋል።
ሆስፒታሉ ከተባባሪ አካላት ባገኘው የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ ህሙማንን ከመኖሪያ አካባቢያቸው ጀምሮ እስከ ሆስፒታል የደርሶ መልስ የመጓጓዣና በቆይታቸውም ነፃ የምግብ አገልግሎት ጭምር እንደሚሰጣቸው አስረድተዋል።
በሰሜን ወሎ ዞን የጉባላፍቶ ወረዳ ቀበሌ 011 ነዋሪ አቶ በዜ ቢረሳው በሰጡት አስተያየት፤ በሁለት ዓይናቸው በተከሰተ የዓይን ሞራ ግርዶሽ ማየት ባለመቻላቸው ሲቸገሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
ዛሬ ላይ በተደረገላቸው ህክምና ብርሃናቸው መመለሱን ገልጸዋል።
በዓይን ብርሃን ማጣት ከቤት መዋሌ ተስፋ አስቆርጦኝ ነበር ያሉት ደግሞ በዞኑ የግዳን ወረዳ ነዋሪ አቶ ደርሶ ይመር ናቸው።
ዛሬ በተደረገላቸው ህክምና የዓይን ብርሃናቸው በመመለሱ ዳግም እንደተወለዱ እንደሚቆጥሩት ተናግረዋል።