ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ አርአያነት ያለው ስራ ሰርተው አልፈዋል-የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች - ኢዜአ አማርኛ
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ አርአያነት ያለው ስራ ሰርተው አልፈዋል-የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች
አዲስ አበባ፤ መስከረም 7/2017(ኢዜአ)፦ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በኢትዮጵያ ማህበራዊ ፍትህ ለማስፈን በሚደረገው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ አርአያነት ያለው ስራ ሰርተው ማለፋቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ባደረባቸው ህመም ምክንያት በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ዛሬ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
የፖለቲካ አመራሮችም በፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸዋል፡፡
ፕሮፌሰር በየነ በኢትዮጵያ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ የነበራቸው ሚና የጎላ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ምክትል ሰብሳቢ ራሄል ባፌ(ዶ/ር) ፕሮፌሰር በየነ በኢትዮጵያ ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል አባት የነበሩና ቋሚ ታሪክ ጽፈው ያለፉ ናቸው ብለዋል።
ማህበራዊ ፍትህን ለማስፈን ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል በማድረግ አገራቸውን በቅንነት በማገልገል አርአያነት ያለው ታሪክ አስቀምጠዋል ነው ያሉት፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች የሰላማዊ ትግል ርዕዮተ-አለምን በመከተል ለአገራቸው መልካም ስራ እንዲሰሩ ያስተማሩ ናቸው ብለዋል።
በትምህርት ዘርፉም የራሳቸውን አሻራ ያሳረፉ በተለይም በባዮሎጂ የትምህርት መስክ በርካታ ምሁራንን ያፈሩ እንደነበሩም አስታውሰዋል።
የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) በበኩላቸው ፕሮፌሰር በየነ በኢትዮጵያ አሉ ከሚባሉ ምክንያታዊና ሰላማዊ የፖለቲካ ታጋዮች መካከል በግንባር ቀደምትነት የመጠቀሱ እንደነበሩ ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የሃሳብ ልዕልናን መሰረት ያደረገ የዴሞክራሲ ባህል እንዲገነባ የበኩላቸውን ሚና ማበርከታቸውንም እንዲሁ፡፡
ማህበራዊ ፍትህን ለማረጋገጥ በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ ለጥቅም የማይገዙና በዓላማቸው የጸኑ ጠንካራ ፖለቲከኛና ምሁር እንደነበሩም ነው የገለጹት።
አገራዊ ለውጡ እንዲመጣ ፕሮፌሰሩ የድርሻቸውን ሚና መወጣታቸውን ገልጸው፤ ለውጡን የተሳካ ለማድረግ በተሰጣቸው የስራ ኃላፊነት በቅንነት ሲያገለግሉ መቆየታቸውንም ነው ዶክተር አረጋዊ የጠቀሱት።
ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ሙያ፤ በመንግስታዊ የስራ መዋቅር ውስጥም በትምህርት ሚኒስትር ዴኤታነት እንዲሁም የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በመሆን ህይወታቸው እስካለፈበት ቀን አገራቸውን አገልግለዋል።