ኢትዮጵያ በቀጣናው እና በአፍሪካ ጉልህ ሚና የምትጫወት አገር ነች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በቀጣናው እና በአፍሪካ ጉልህ ሚና የምትጫወት አገር ነች
አዲስ አበባ፤ መስከረም 7/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በቀጣናው እና በአፍሪካ ጉልህ ሚና የምትጫወት አገር መሆኗን የፈረንሳይ ምክር ቤት የአፍሪካ ቀንድ ወዳጅነት ቡድን አባላት ገለጹ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ በሴናተር ሂዩግ ሶሪ ፕሬዝዳንትነት የተመራውን የፈረንሳይ ፓርላማ የአፍሪካ ቀንድ ወዳጅነት ቡድን አባላትን በጽህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል።
ሚኒስትሩ ለፓርላማ አባላቱ የኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ ግንኙነት ታሪካዊ እና ረጅም ዘመን ያስቆጠረ መሆኑን በመግለጽ፤ ፈረንሳይ በኢትዮጵያ በልማት ትብብር፣ በባህል፣ በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዙሪያ የምታደርገውን ተሳትፎ አድንቀዋል።
ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የምትገኝበት ቀጣና መልከዓ ምድራዊ እና ስትራቴጂካዊ አቀማመጡ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያለው በመሆኑ የበርካታ አካላትን ትኩረት የሳበ መሆኑን ለፓርላማ አባላቱ ገልጸዋል።
አምባሳደር ታዬ ኢትዮጵያ ካላት ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር እና እያደገ ከመጣው ምጣኔ ሀብቷ አኳያ ባሕር በር ወሳኝ በመሆኑ በሰጥቶ መቀበል መርህ በሰላማዊ መንገድ ለማግኘት እያደረገችው ያለውን ጥረት አብራርተዋል።
በሶማሊያ ከድህረ አትሚስ በኋላ የሚኖረው የኃይል ስምሪት በጥንቃቄ መታየት እንደሚገባው ለሴናተሮቹ መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
የፓርላማ አባላቱ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በቀጣናው እና በአፍሪካ ጉልህ ሚና ያላት አገር መሆኗን በመግለጽ የኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ መጠናከር እንደሚገባውም በውይይታቸው ላይ አንስተዋል።