በኦሮሚያ ክልል የ2017 የትምህርት ዘመን ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል የ2017 የትምህርት ዘመን ተጀመረ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 7/2017(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የ2017 የትምህርት ዘመን በሁሉም የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች ዛሬ ተጀምሯል።
በሸገር ከተማ አስተዳደር ፉሪ ክፍለ ከተማ በኩራቡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የ2017 የትምህርት ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሄዷል፡፡
በመርኃ ግብሩ ላይ የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ቡልቶሳ ሂርኮ፣ የሸገር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ግርማ ሃይሉ፣ የሸገር ከተማ አስተዳዳር ትምህርት ጽህፈት ቤት ሃላፊ ፊራኪያ ካሳሁንና ሌሎች የትምህርቱ ማህበረሰቦች ተገኝተዋል።
የቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ቡልቶሳ ሂርኮ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ጥራትን በማስጠበቅ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ የተማሪዎች ውጤት መሻሻል እያሳየ መሆን ገልጸው፤ ወደ ሚፈለገው ደረጃ ለማሳደግ በዘንድሮ የትምህርት ዓመት የባለ ድርሻ አካላት ተሳትፎ ይበልጥ እንዲጠናከር ጠይቀዋል፡፡
በተለይም ወላጆች ልጆቻቻው ውጤታማ እንዲሆኑ ትምህርት ቤት ከመላክ ባለፈ የተማሩትን በአግባቡ አጥንተው ውጤታማ እንዲሆኑ ጊዜ ሊሰጡ ይገባል ብለዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል የ2017 ዓም የትምህርት ዘመን በሁሉም የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች መጀመሩን ገልጸዋል።