ቀጥታ፡

የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን ለተፋሰሱ ሀገራት አዲስ የትብብር ምዕራፍ ይከፍታል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 7/2017(ኢዜአ)፦ ሊቋቋም የመጨረሻ ምእራፍ ላይ የሚገኘው የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን የቅኝ ግዛት ውሎችን ውድቅ በማድረግ ለተፋሰሱ ሀገራት አዲስ የትብብር ማዕቀፍ እንደሚከፍት ኢዜአ ያነጋገራቸው የውሃና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁራን ገለጹ፡፡

የናይል ተፋሰስ አገራት የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ሰነድ እ.አ.አ በ2010 ለፊርማ ክፍት የሆነ ሲሆን ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛንያና ዩጋንዳ፣ ደቡብ ሱዳንና ብሩንዲ ፈርመውታል።

ደቡብ ሱዳን በቅርቡ ማዕቀፉን በፓርላማዋ ያፀደቀች ስድስተኛ አገር ሆናለች። ይህም ማዕቀፉን ወደ ተፈጻሚነት ምዕራፍ አሸጋግሮታል።

በስምምነት ማዕቀፉ እንደተመላከተው ከተፋሰሱ አገራት ቢያንስ ስድስት አገራት በፓርላማቸው አጸድቀው ለአፍሪካ ህብረት ካስገቡ የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን ማቋቋም ይችላሉ።

ይህ የሚቋቋመው ኮሚሽን የናይል ወንዝ አጠቃቀምና አስተዳደር ላይ ሕጋዊ መሰረት የሚጥል በመሆኑ በተፋሰሱ ፍትሃዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም እንዲኖር ሚናው ከፍተኛ እንደሆነ ይታመናል።

በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተመራማሪው ሰይድ አህመድ (ዶ/ር) የኮሚሽኑ መቋቋም በቀጣናው ፍትሃዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም እንዲኖርና የቀጣናውን ሰላም ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን አስቀድማ በመፈረምና በፓርላማዋ በማጽደቅ ከተፋሰሱ አገራት ጋር አብሮ የመልማት ፍላጎቷን ማሳየቷን አውስተዋል።

ፍትሃዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም ላይ የተፋሰሱ አገራት ተመሳሳይ እሳቤና አቋም እንዲኖራቸው የኮሚሽኑ መቋቋም ሚናው የጎላ መሆኑንም ነው የጠቀሱት።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ እያደረገች ያለው ጥረት ለሌሎች ምሳሌ የሚሆንና በአገራት ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ ነው ብለዋል።

እ.አ.አ በ1929 እና በ1959 የተፈረሙት የቅኝ ግዛት ውሎች የላይኞቹን ተፋሰስ አገራት ታሳቢ ያላደረጉና ተቀባይነት የሌላቸው መሆኑንን ነው ተመራማሪው የገለጹት።

የኮሚሽኑ መቋቋም የቅኝ ግዛት ውሎች ውድቅ በማድረግ በተፋሰሱ አዲስ የትብብርና አብሮ የመልማት ምዕራፍ ይከፍታል ነው ያሉት።

የቀድሞ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ቡድን አባልና የውሃ ሃብት ተመራማሪው ፈቅ አህመድ ነጋሽ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በናይል ትብብር ስምምነት ማዕቀፍም ሆነ በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ከተፋሰሱ አገራት ጋር በስምምነት ለመስራት ያላትን ፍላጎት በግልጽ እያሳየች መጥታለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ በጋራ የውሃ ሃብቶች ላይ ፍትሃዊና ምክንያታዊ አጠቃቀም እንዲኖርና በጋራ መልማት ላይ ያላትን ጽኑ አቋም በተደጋጋሚ ለዓለም ማሳየቷን ገልጸዋል።

የናይል ተፋሰስ ትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን እውን ለማድረግ ከአስር ዓመታት በላይ ጥረቶች ሲደረጉ እንደነበር አስታውሰው፣በቅርቡ ደቡብ ሱዳን ስምምነቱን ማጽደቋን ተከትሎ ኮሚሽን ማቋቋም የሚያስችል ደረጃ ላይ ደርሷል ብለዋል።

ይህ ኮሚሽን በጋራ ሃብት ላይ እኔ ብቻ ልጠቀም የሚል የቆየና ያረጀ አስተሳሰብን ውድቅ የሚያደርግና የተፋሰሱ አገራት በጋራ መልማትና ማደግ የሚችሉበትን አቅጣጫ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

የሚቋቋመው ኮሚሽን በተፋሰሱ ዘላቂ ሰላምና ልማት የሚያረጋግጥ እንዲሆን ኢትዮጵያ የመሪነት ሚናዋን አጠናክራ መቀጠል እንዳለባትም ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም