ቀጥታ፡

መንግስት የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ ቱሪዝምን ጨምሮ ወሳኝ የልማት ዘርፎች ላይ አበክሮ እየሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 7/2017 (ኢዜአ):- መንግስት የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ ቱሪዝምን ጨምሮ ወሳኝ የልማት ዘርፎች ላይ አበክሮ እየሰራ እንደሚገኝ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በረከት ፍስሐጽዮን ገለጹ።

ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የዓለም ቱሪዝም ቀንን አስመልክቶ ከቱሪዝም ሚኒስቴርና ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር እየተካሄደ ባለው የቱሪዝም መድረክ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ነው።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በረከት ፍስሀጽዮን መንግስት የኢትዮጵያን ዕምቅ ፀጋዎች ለይቶ በማልማትና እሴት በመጨመር ኢኮኖሚያዊ እምርታን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

ቱሪዝም በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ከተመላከቱ 5 ቁልፍ የኢኮኖሚ ዘርፎች መካከል መሆኑን ገልፀዋል።

ዘርፉ ስራ ዕድል ፈጠራና የዜጎች ኑሮ ማሻሻያ ጉልህ ሚና እንዳለው ጠቁመው፤ በዕለቱ ይፋ የተደረገው የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ሚናውን እንደሚያጠናክረው አንስተዋል።

በሌላ በኩል በአገልግሎት ዘርፉ የሚገኘውን ገበያ የሚያሻሻል፣ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ብሎም በዘርፉ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች መፍትሔ ለማበጀት ያግዛልም ነው ያሉት።

መንግስት አሁንም በዘርፉ እምርታ የሚጨምሩ የፖሊሲና አሰራር እርምጃዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ(ዶ/ር) በበኩላቸው የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት የቱሪዝም ዘርፉን አንድ ደረጃ ወደ ፊት የሚያራምድ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምት፣ የሰው ዘር መገኛ፣ የፓን አፍሪካ ንቅናቄ መሰረት የህብረብሄራዊነት መገለጫ መሆኗን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ እነዚህ እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶቿን፣ ባህልና ወጎቿን በተደራጀ መንገድ አገልግሎት ላይ ማዋል ሳትችል ቆይታለች ብለዋል።

የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ቀጣይነት ያለውና የማያቋርጥ የተደራጀ የቱሪዝም ስታስቲክስ መረጃ በመያዝ የተሳለጠ የቱሪዝም መረጃ ፍሰት እንዲኖር ያስችላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም