በትግራይ ክልል ለግብርና ናሙና ቆጠራ ስራ ለተመለመሉ ወጣቶች የሙያ ስልጠና እየተሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል ለግብርና ናሙና ቆጠራ ስራ ለተመለመሉ ወጣቶች የሙያ ስልጠና እየተሰጠ ነው
መቀሌ፣መስከረም 7/2016(ኢዜአ)፦በትግራይ ክልል በ2017 ዓ.ም በግብርና ናሙና ቆጠራ ስራ የሚሳተፉ ከአንድ ሺህ በላይ ወጣቶች የሙያ ስልጠና እየተሰጣቸው መሆኑን የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት አስታወቀ፡፡
በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የመቐለ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ አብርሃ መሰለ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በግብርና ናሙና ቆጠራ የሚሳተፉ ከሁሉም የትግራይ አካባቢዎች የተውጣጡ ከአንድ ሺህ በላይ ወጣቶች የአቅም ግንባታና የግንዛቤ ማጎልበቻ ስልጠና እየወሰዱ ናቸው።
አገልግሎቱ ለስልጠናው የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያሟላ ሲሆን፤ "ስልጠናው በትግራይ በሚገኙ አራት ዩኒቨርሲቲዎች እየተሰጠ ይገኛል" ብለዋል፡፡
የናሙና ቆጠራው ለግብርናው ዘርፍ ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎችን ለመሰብሰብ እና በዘርፉ ያሉ ሃብቶችንና ክፍተቶችን ለማጥናት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
"እየተሰጠ ያለው ስልጠና በቴክኖሎጂ የተደገፈ በመሆኑ ሰልጣኞች በቀላል መንገድ አቅማቸውን የሚያዳብሩበት ይሆናል" ብለዋል፡፡
ከ22 ዓመት በኋላ የሚካሄደው የናሙና ቆጠራ የመረጃ ክፍተትን በመሙላት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም አገልግሎቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
የናሙና ቆጠራው ከተያዘው ወር ጀምሮ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ የሚካሄድ መሆኑን አመልክተዋል።
በናሙና ቆጠራውም የእርሻና የእንስሳትን ጨምሮ ግብርና ነክ ሃብቶች በሙሉ የሚመዘገቡ መሆኑን ገልፀው፤ሥራውም በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ተግባራዊ እንደሚደረግም አስረድተዋል፡፡
በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና እና የስራ እድል ፈጠራ ቢሮ የስራ እድል ፈጠራና የኢንተርፕራይዝ ልማት ዳይሬክተር አቶ በርሀ ፀጋይ በበኩላቸው፤ የግብርና ናሙና ቆጠራ ሥራው ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡
በዚህ ዘርፍ ብቻ በትምህርት ደረጃ የተለዩ ከ1 ሺህ 600 በላይ መረጃ ሰብሳቢዎች፣ አስተባባሪዎች እና ሱፐርቫይዘሮች የስራ እድል እንደሚያገኙም አመልክተዋል፡፡
አገልግሎቱ የግብርና ናሙና ቆጠራ ሥራ ለተመለመሉ ወጣቶች በመቀሌ፣ በአክሱም፣ በራያና በአዲግራት ዩኒቨርሲቲዎች ስልጠና እየሰጠ ይገኛል።