በክልሉ የሚገኙ የመሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን አደረጃጀት ለማጠናከር የሚያስችል የሪፎርም ስራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የሚገኙ የመሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን አደረጃጀት ለማጠናከር የሚያስችል የሪፎርም ስራ እየተከናወነ ነው
ሚዛን አማን ፤ መስከረም 07/2017 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የሚገኙ የመሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራት አደረጃጀትን ፍሬያማ ለማድረግ የሚያግዝ ሪፎርም እየተሠራ መሆኑን የክልሉ ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ አስታወቀ።
እየተሰራ ያለው ሪፎርም ማኅበራቱ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ ሁኔታን ከግምት ውስጥ ያስገባ ተግባር እንዲያከናውኑ የሚያስችላቸው መሆኑም ተገልጿል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ቀበሌ መንገሻ ለኢዜአ እንዳሉት በክልሉ 2 ሺህ 50 መሠረታዊ የኅብረት ስራ ማህበራትና 21 ዩኒየኖች አሉ።
እነዚሁ መሰረታዊ የህብረት ስራ ማህበራት በተቀናጀ መንገድ የአባላቸውን ተጠቃሚነት ማሳደግ እና በኢኮኖሚው ላይ ያላቸውን ሚና ማላቅ እንዲችሉ የሪፎርም ስራው ማስፈለጉን ተናግረዋል።
በዚህም የኅብረት ሥራ ማኅበራቱ ያለባቸውን የአመራር፣ የአሰራር እና የሰው ኃይል አደረጃጀት ክፍተቶችን በመሙላት በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ጉልህ ሚና እንዲኖራቸው ማስቻል ነው ያሉት።
ማህበራቱ ምርታማነትን ማሳደግና ተጠቃሚነትን ማላቅ ዓላማ ያደረገ እንቅስቅሴ እንዲኖራቸው ለማስቻል ጠንካራ አደረጃጀት መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም አሠራራቸውን ሪፎርም የማድረግ ስራ በልዩ ትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በተያዘው ዓመት በክልሉ ከሚገኙት ማህበራት ከ1 ሺህ በላይ የሚሆኑትን ማኅበራት አቋም የመፈተሽና አሠራርና አደረጃጀታቸውን የማሻሻል ሥራ ይሠራል ብለዋል።
በሂደቱም በስም ብቻ ያሉና የተቀመጠውን ደረጃ የማያሟሉ፤ አባላቸውንም ሆነ ለማህበረሰቡ ከመጥቀም አንጻር ጉድለት የሚታይባቸውን የማፍረስና ከሌሎች ጋር የማዋሄድና የማጠናከር ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በክልሉ ውስጥ ካሉ 2 ሺህ 50 መሠረታዊ የህብረት ማኅበራት ውስጥ እስካሁን 900 የሚሆኑትን ለሪፎርሙ ሥራ የመለየት ሥራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።
ማኅበራቱን በተመሳሳይ የአደረጃጀት ዘርፍ ሰብሰብ በማድረግ በብድርና ቁጠብ እየተጠናከሩ ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገሩ ኤጀንሲው ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ድጋፍና ክትትል ያደርጋል ብለዋል።
ዘንድሮ ሪፎርም ከሚደረጉ 1 ሺህ ማኅበራት ውጭ ያሉት ደግሞ በቀጣይ ዙር እንደሚታዩ ገልጸው፤ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ 21 ዩኒየኖችም የዚሁ ሪፎርም አካል እንደሚሆኑ አክለዋል።
የቤንች ማጂ አንድነት ሁለገብ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ አቶ ፈተና ሺፋ በበኩላቸው ሪፎርሙ በብዙ መልኩ ኢኮኖሚያዊ ለውጥን ለአርሶ አደሩና ለአባላቱ ያመጣል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ማኅበራት ካልተጠናከሩ ዩኒየኖች ምርት አግኝተው ማገበያየትና በዓለም አቀፍ ደረጃ መጠናከር እንደማይችሉ ገልጸው፤ መሠረታዊ የህብረት ሥራ ማኅበራት ያሉበትን ደረጃ ፈትሾ የማሻሻል ተግባሩን ዩኒየኑ እንደሚደግፍ ገልጸዋል።
እንደ ዩኒየኑም ሪፎርሙን ተቀብሎ የሚሰጠውን የአሠራር ማሻሻያ ለመተግበር ዝግጁ እንደሆኑም እንዲሁ።
በሰሜን ቤንች የያሊ መሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ ቄስ ፍቃዱ ዳምጤ እንዳሉት 143 አባላትን በመያዝ በቡና እና የፍጆታ ምርት አቅርቦት ላይ እየሠሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አሁን የሚደረገው ሪፎርም የባንኮችን የብድር አቅርቦት እና የግብይት ትስስርን በመፍጠር ወደ ላቀ ደረጃ ያደርሳል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸው፤ "የምርት መጠንና ጥራትን ማሳደግ ላይ በትኩረት እንሰራለን" ብለዋል።