ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሳተላይት አካውንት በዘርፉ የነበረውን የተደራጀ መረጃ ውስንነት መፍታት የሚያስችል ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 07/2017 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሳተላይት አካውንት በዘርፉ የነበረውን የተደራጀ መረጃ ውስንነት መፍታት የሚያስችል መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ገለጹ።

የዓለም የቱሪዝም ቀንን በማስመልከት ከኢጋድና ከተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ጋር በመተባበር የተዘጋጀው ኤግዚቢሽን በዐድዋ ድል መታሰቢያ ተጀምሯል።


 

የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በዚህ ወቅት እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ በታሪካዊ፣ በተፈጥሯዊና ባህላዊ ሀብቶች እንዲሁም በቱሪዝም መዳረሻዎች የበለጸገች ነች።

ኢትዮጵያውያን የአብሮነት መሰረታቸው ባህላቸውና ወጋቸው የዓለም ጎብኝዎችን ትኩረት በመሳብ ለዓመታት ዘልቋል።

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የቱሪዝም አቅም በመሰረተ ልማት ማበልፀግ ባለመቻሏ ከዘርፉ የሚገባትን ጥቅም ሳታገኝ ቆይታለች ብለዋል።

ከለውጡ በኋላ መንግሥት ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት በመስጠት ቱሪዝምን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ቱሪዝም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መሰረታዊ በሆነ መንገድ መቀየር የሚችል አቅም እንዳለው ገልጸው፤ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የቱሪዝም ዘርፉን ለማዘመን እየተሰራ ነው።

ቱሪዝም የውጭ ምንዛሪ በማሳደግና የሥራ ዕድል በመፍጠር የጎላ አበርክቶ እንዳለው ጠቅሰው፣ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ለጎብኚዎች የተደራጀ መረጃ በመስጠት የተሳለጠ አገልግሎት ማግኘት ያስችላል ብለዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሳተላይት አካውንት በዘርፉ የነበረውን የተደራጀ መረጃ ውስንነት በመፍታት ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት ዛሬ ማለዳ ይፋ መሆኑ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም