ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በፍትሐዊ ተጠቃሚነት መርህ የአፍሪካን የድህነት ታሪክ መቀየር እንደሚቻል ትምህርት የሚሰጥ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በፍትሐዊ ተጠቃሚነት መርህ የአፍሪካን የድህነት ታሪክ መቀየር እንደሚቻል ትምህርት የሚሰጥ ነው
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 07/2017 (ኢዜአ)፡- የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በፍትሐዊ ተጠቃሚነት መርህ የአፍሪካን የድህነት ታሪክ መቀየር እንደሚቻል ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን የታሪክ ተማራማሪው ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ ገለጹ።
ፕሮፌሰር አህመድ ፤ ታላቁ የህዳሴ ግድብ አፍሪካ የተፈጥሮ ሃብቶቿን በራሷ አቅም ማልማት እንድምትችል አብነት የሆነ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
ግድቡ ከኢትዮጵያ ባለፈ ለቀጣናውና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትን በኃይል በማስተሳሰር ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በዘመናት ታሪኳ ውስጥ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ላይ ጽኑ አቋም እንዳላት ጠቅሰው፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም የዚሁ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ባከበረ መልኩ ግድቡን ወደ ማጠናቀቅ እየተጓዘች መሆኗን ጠቁመው፤ በዚሁ ሁሉ ሂደት ውስጥ በየትኛውም ሀገር ላይ ጉዳት እንደማታደርስ በተግባር ማሳየቷን ገልጸዋል፡፡
የአፍሪካ የድህነት ታሪክ የሚቀየረው መሰል ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን መሰረት ባደረጉ ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶች እንደሆነም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ አፍሪካን በመሰረተ ልማት በማስተሳሰር ረገድ አብነት የሆነ ተግባር እያከናወነች መሆኑን ነው ፕሮፌሰር አህመድ የገለጹት።
ኢትዮጵያ ከግድቡ ግንባታ በተጓዳኝ በአረንጓዴ አሻራ አማካኝነት የታችኛው ተፋሰስ ሀገራትን ተጠቃሚ የሚያደርግ የአካባቢ ጥበቃ ስራ እያከናወነች መሆኑን አመልክተዋል።
ችግኞችን ወደ ጎረቤት ሀገራት በመላክ ጭምር ቀጣናው ከመሰረተ ልማት ባሻገር በአካባቢ ጥበቃ ስራ እንዲተሳሰር የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች ነው ብለዋል።
ከዚህ አኳያ በግድቡ ላይ የተሳሳተ መረጃ የሚያሰራጩ ሀገራት ሁሉንም ተጠቃሚ በሚያደርገው የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባም ተናግረዋል።