በክልሉ "መልካም" የተባለውን ማሽላ የማስፋፋት ስራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ "መልካም" የተባለውን ማሽላ የማስፋፋት ስራ እየተከናወነ ነው

ሐረር ፤ መስከረም 7/2017 (ኢዜአ):- በሐረሪ ክልል "መልካም" የተባለውና ከፍተኛ ምርት የሚሰጠውን ማሽላ የማስፋፋት ስራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ እየለማ የሚገኘውና "መልካም" የተባለው የማሽላ ዝርያ በአርሶ አደሮችና በግብርና ባለሙያዎች እየተጎበኘ ነው።
በክልሉ ግብርና ቢሮ የግብርና ኤክስቴንሽን ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ሬድዋን በጉብኝቱ ወቅት እንደገለፁት፤ "መልካም" የተሰኘው የማሽላ ዝርያ በክልሉ በ800 ሄክታር መሬት ላይ በኩታ ገጠም እየለማ ነው።
የማሽላ ዝርያው የዝናብ እጥረትንና በሽታን በመቋቋም በሄክታር እስከ 43 ኩንታል ምርት መስጠት የሚችል መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም ቀደም ሲል ከነበረው የማሽላ ዝርያ ከእጥፍ በላይ ብልጫ እንዳለው ገልፀዋል።
የማሽላ ዝርያውን በክልሉ አሁን የተሸፈነውን ማሳ ወደ 6ሺህ 337 ሔክታር መሬት ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
የማሽላ ዝርያውን መስፋት የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እየተከናወነ የሚገኘውን ስራ ስኬታማ ማድረግ እንደሚያስችልም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
የጉብኝቱ ዓላማም አርሶ አደሩ ልምድና ተሞክሮ በመውሰድ የማሽላ ዝርያውን በአካባቢው እንዲያስፋፋ ታስቦ መሆኑን አክለዋል።
በመስክ ጉብኝቱም የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ነስረዲን አህመድ፣ አርሶ አደሮች፣ የግብርና ባለሙያዎች፣ ተመራማሪዎች፣ ወጣቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።