ኢንተርፕራይዙ የገረብ ሰገን ግድብን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት የማሻሻል ተግባር እያከናወነ መሆኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ኢንተርፕራይዙ የገረብ ሰገን ግድብን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት የማሻሻል ተግባር እያከናወነ መሆኑን ገለጸ

መቀሌ፤ መስከረም 07/2017 (ኢዜአ)፡-የገረብ ሰገን ግድብን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት የማሻሻልና ለመስኖ ልማት አገልግሎት እንዲውል የማድረግ ተግባር እያከናወነ መሆኑን በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የውሃ ሥራዎች ዲዛይን ቁጥጥርና ክትትል ኢንተርፕራይዝ ገለጸ።
በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የውሃ ሥራዎች ዲዛይን ቁጥጥርና ክትትል ኢንተርፕራይዝ ኃላፊ መሓሪ ገብረዮሃንስ(ዶ/ር) እንደገለፁት፤ ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የገረብ ሰገን ግድብ በዓመት 25 ሚሊዮን ሜትር ኩብ የውሃ መጠን ይይዛል።
ግድቡ በየዓመቱ ከሚይዘው የውሃ መጠን 20 በመቶው ብቻ ለንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እየዋለ መሆኑን ገልፀዋል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ግድቡ በየአመቱ የሚይዘውን የውሃ መጠን ሙሉ በሙሉ ጥቅም ላይ እንዲውል ተጨማሪ ስራዎች እንዲሰሩ መወሰኑን ገልፀዋል።
የፌዴራል መንግስት በግድቡ ግንባታ ላይ የሙያና የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉን ያስታወሱት ኃላፊው፤ በመቀሌ ከተማ ያለውን የንፁህ መጠጥ ውሃ እጥረት ለማቃለል የሚደረገውን ጥረት ህዝቡ እንዲደግፍም ጠይቀዋል።
በግድቡ ዙሪያ ቀሪ የጂኦሎጂ ዝርዝር ጥናት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በኢንተርፕራይዙ ከፍተኛ የውሃ ምህንድስና ባለሙያ አቶ ሰሎሞን ተክኤ ናቸው።
ጥናቱን በማጠናቀቅ ግድቡ በሚይዘው የውሀ መጠን ልክ የተሟላ የመጠጥና የመስኖ አገልግሎት እንዲሰጥ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በኢንተርፕራይዙ የውሃ ምህንድስና ባለሙያው አቶ ግርማይ ተጫነ በበኩላቸው የግድቡ ግንባታ ሲጀመር 500 ሄክታር መሬት ለማልማት ታስቦ እንደነበር ገልፀው፤ በሂደት ለከተማው የመጠጥ ውሃ አገልግሎት እንዲሰጥ በመደረጉ ለመስኖ ልማት እንዲያመቹ ተደርገው የተገነቡት የውሃ ማፋሰሻዎች ስራ ሊጀምሩ አለመቻላቸውን አስረድተዋል።
ሆኖም ይህንኑ ችግር በማስተካከል የአካባቢው አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ከግድቡ ወደ ከተማው ተጨማሪ ውሃ ለመግፋት የሚያስችል የውሀ መስመር የማስገባትና የግድቡን ዘላቂነት የማረጋገጥ የአፈር መከላከልና ሌሎች የጂኦሎጂ ጥናት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውም ተገልጿል።